(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 24/2011) በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እንዲቆም ለመጠየቅ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ
በተለያዩ ከተሞች የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል፡፡
የሰልፉ ትኩረት በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የአማራ መፈናቀል እና ሞት ይቁም የሚል ነው ተብሏል።
የአማራ ክልል ርእሰ ከተማ ባህር ዳር ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ መነሻውን በተለምዶ ገበያ አካባቢ በማድረግ መድረሻውን ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት በማድረግ በሰላም ተጠናቋል።
ሰልፈኞቹ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ በማሰማት በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ በተለያዩ አካባቢዎች እየደረሰ ያለው ሞትና ሰቆቃ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (አዴፓ) በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን ሞት እና እንግልት እንዲያስቆምም አሳስበዋል፡፡
የባሕር ዳር ሰልፈኞች ካስተላለፏቸው መልዕክቶች መካከል ‹የአማራ መፈናቀል እና ሞት ይቁም! ‹ፍትሕ ለወልቃይት፣ ለመተከል፣ ለራያ እና ለደራ አማራዎች! ‹የአማራ መደራጀት ቅንጦት ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ ነው የሚል ይገኝበታል።
ሰልፈኞቹ አዴፓ ስሙን ሳይሆን ግብሩን ይቀይር የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል። ሕገ መንግሥቱ አማራን የማይወክል በመሆኑ በአማራ ሕዝብ ተቀባይነት የለውም ያሉም ነበሩ።
ሰልፈኞቹ በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት አካባቢ በመገኘት የሚመለከታቸው ሁሉ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡም አሳስበዋል፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላምና ደምበጫ ከተሞችም ተመሳሳይ ተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
የፍኖተሰላምና ደምበጫ ከተማ ነዋሪዎች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያና ማፈናቀል በጽኑ አውግዘዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ተገቢውን ድጋፍና ጥበቃ ለክልሉ ተወላጆች እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡
ሰልፈኞቹ ‹‹በመተከልና አጣዬ የተፈጸመውን ግድያ እናወግዛለን፣ የአማራ ሕዝብ ፍትሕ ማግኘት አለበት፣ ለደረሠው ጥቃት መንግሥት ተጠያቂ ነው›› የሚሉ መልዕክቶችን ነው ያስተላለፉት፡፡
የደብረ ማርቆስ የደጀን እና የደብረታቦር ከተሞች አስተዳደር ነዋሪዎች እንዲሁ ተመሳሳይ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደው በሰላም አጠናቅቀዋል፡፡
በሰላማዊ ሰልፉም ‹‹የአማራ ሕዝብ መፈናቀልና ግድያ ይቁም፣ በመተከል አውራጃ የሚጨፈጨፉ ዜጎችን ሕይወት መንግሥት ሊታደግ ይገባል›› የሚሉና ሌሎችኝም መልዕክቶች አስተጋብተዋል።
በተመሳሳይ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ብሔር ላይ እየደረሰ ያለውን ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት መንግሥት እንዲያስቆም በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ከተማ ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል፡፡