(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 23/2011)በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የተከሰተው የጸጥታ ችግር በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።
ነዋሪዎች ግን አሁንም የጸጥታው ችግር እንደቀጠለ መሆኑን መግለጻቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አበራ ባየታ ለኢሳት እንደገለጹት ባለፉት አራት ቀናት የነበረው ችግር አሁን ሙሉ በሙሉ ቆሟል።
በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የሚመራ የመንግስት ሃላፊዎች ቡድን ችግሩ ወደተከሰተበት አከባቢ ማምራቱን የገለጹት አቶ አበራ የማረጋጋት ስራው በተሳካ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ነው ብለዋል።
ይሁንና በአንዳንድ አከባቢዎች ስጋት እንዳለ የሚያሳዩ መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው። በተለይም በፓዌና ማምቡክ ወረዳዎች ችግሩ አልተቀረፈም የሚሉ ነዋሪዎች ዛሬ የአንድ ሰው ህይወት የጠፋበት ግጭት መከሰቱን ገልጸዋል።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አበራ ባየታ ግን ሰላሙ ተሻሽሏል፡ ግጭቱም ሙሉ በሙሉ ቆሟል ይላሉ።