በከሚሴ ለተፈጸመው ጥቃት ዘላቂ መፍትሄ ካልተሰጠው ዳግም ሊከሰት እንደሚችል ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 3/2011)በከሚሴ ለተፈጸመው ጥቃት ዘላቂ መፍትሄ ካልተሰጠው ዳግም ሊከሰት እንደሚችል ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገለጹ።

የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት እንደዘገበው ከሰሞኑ የተነሳው ግጭት ወደ ስፍራው በገባው የፀጥታ ኃይልና በአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍ ቢረጋጋም ለጉዳዩ ዘላቂ እልባት እስካልተሰጠው ድረስ ከስጋት ነፃ መሆን እንደማይችሉ የከሚሴ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ፋይል

የጥቃቱ መነሻ በአሉባልታ ሰለባ የሆነው የወረዳው አመራር መሆኑን የሚገልጹት ነዋሪዎች አሁንም አመራሩ ህዝቡ ላይ ስጋት ደቅኖ ይገኛል ብለዋል።

የኦሮሞንና የአማራን ህዝብ ለማጋጨት ታቅዶ የተፈጸመው ጥቃት ጉዳት ቢያደርስም የክፋት ዓላምው ግን መቼም አይሳካም ሲሉም ገልጸዋል የከሚሴ ነዋሪዎች።

ወሎ ከሚሴን፣ ሰሜን ሸዋ አጣዬንና ማጀቴን ሲያስጨንቅ የነበረው የሶስት ቀናቱ አለመረጋጋት አሁን ላይ ጋብ ማለቱ ይነገራል።

በሰሜን ሸዋ አስተዳደር መረጃ መሰረት የ27 ሰዎችን ህይወት ያጠፋው ጥቃት ዓላማው በኢትዮጵያውያን መካከል ደም ለማቃባት የታለመ ነበር።

የክልልና የፌደራል መንግስታት ጉዳዩን በማጣራት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ድርጊቱ ዳግም እንዳይከሰት አስፈላጊውን ርምጃ እንደሚወስድ መንግስት ቢያስታውቅም የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ግን ከስጋት ሊላቀቁ አልቻሉም።

የአማራ  መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ያነጋገራቸው የከሚሴ ነዋሪዎች እንደሚሉት ጠባሳ ትቶ ያለፈው የሰሞኑ ጥቃት ዳግም ላለመከሰቱ ዋስትና የለም።

ነዋሪዎቹ የወረዳቸው አመራሮች የችግሩ መነሻ እንደሆኑ በመጥቀስ በአሉባልታ የተሸነፉት የአካባቢው አመራሮች ሌላ ዙር አደጋ በአካባቢው ላይ ደቅነዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ከሚሴ የሁሉም ናት። ሙስሊሙና ክርስቲያኑ፣ ኦሮሞው አማራውና አርጎባው ተከባብረው የሚኖሩባት የሰላምና የፍቅር ከተማ ናት የሚሉት ነዋሪዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አብሮ የመኖር እሴትና አንድነት የሚፈታተኑ አደጋዎች ተከስተዋል ሲሉ ምሬታቸውን ይገልጻሉ።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ሊፈርስ ነው፤ ለዘመናት ዕውቅና ያገኘው ማንነታችሁም አደጋ ውስጥ ሊገባ ነው- የሚለው አሉባልታ የአካባቢውን አመራር አሸንፎታል የሚሉት ነዋሪዎች ዳግም ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል ምልክቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያረጋግጠውም ለቀናት የዘለቀው ጥቃት መቆሙ ለነዋሪው ጊዜያዊ እፎይታን ሰጥቷል።

ሆኖም በአካባቢዎቹ አሁንም ስጋቱ እንዳልተቀረፈ ለማወቅ ተችሏል።

ጥቃቱን ያደረሱ ሃይሎች በቅርበት የሚገኙና ፍጥጫው እንዳለ የሚገልጹት ነዋሪዎች ዳግም ግጭቱ ሊቀሰቀስ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው ማለታቸው ተመልክቷል።

በአጣዬና ማጀቴ ተመሳሳይ ስጋት መኖሩን የሚገልጹት ነዋሪዎች ለጊዜው የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በመኖራቸው መረጋጋት መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

የከሚሴ ነዋሪዎች ለአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት በሰጡት አስተያየት  ለጉዳዩ ዘላቂ እልባት እስካልተሰጠው ድረስ ከስጋት ነፃ መሆን እንደማይችሉ ገልጸዋል።

የአሉባልታ ሰለባ የሆነው የወረዳው አመራር የችግሩ ምክንያትና ተሳታፊም ነው ብለዋል ከሚሴዎች።

ህዝብ ከህዝብ ጋር አልተጋጨም የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች ሰላምና መረጋጋቱን እያደፈረሱ እንደሆነ የሚገልጹት የከሚሴ ነዋሪዎች መንግስት በትኩረት እንዲመረምረው ጠይቀዋል።

አንድ የእስልምና ሃይማኖት አባት የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ሕዝብ የየትኛውም የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች መጠቀሚያ አይደለም ማለታቸውን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል።