በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 3/2011) በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ተገለጸ።

ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ በፍጥነት በመዛመት የፓርኩን ሰፊ ክፍል ማዳረሱ ታውቋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ባለስልጣናት የፌደራል መንግስቱ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር ለማስመጣት መንግስት በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ቀደም ሲል ተከስቶ በነበረው ቃጠሎ ከ300 ሄክታር በላይ የፓርኩ ክፍል በእሳት መውደሙን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከትላንት ጀምሮ በድጋሚ የተቀሰቀሰውን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም የአካባቢው ነዋሪና የጎንደር ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በመረባረብ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የትምህርትና ሳይንስ ተቋም ዩኔስኮ ከመዘገባቸው ድንቅ የተፈጥሮ አካባቢዎች አንዱ ነው።

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የዱር እንስሳት ቀይ ቀበሮ፣ ዋልያና ጭላዳ ዝንጀሮ መኖሪያቸውን ያደረጉበት ስፍራ ነው።

ኢትዮጵያ ካሏት የቱሪስት መስህብ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስም ነው- የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ።

ካለፈው ወር መጨረሻ አንስቶ ይህ የተፈጥሮ መስህብ የሆነ ስፍራ አደጋ ውስጥ ገብቷል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ህልውናውን የሚያጠፋ የእሳት ቃጠሎ ተከስቶ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የሚገልጹት።

ለሁለተኛ ጊዜ ሰኞ ዕለት የተነሳው የእሳት ቃጠሎ የፓርኩን ሰፊ የሳር ሜዳ ለብልቦ መጨረሱን የጠቀሱት ነዋሪዎች በፍጥነት በመዛመት ፓርኩ ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት እያስከተለ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት በደረሰው ቃጠሎ 342 ነጥብ 9 ሔክታር የፓርኩ መሬት በእሳቱ ወድሟል ተብሏል።

የአሁኑ ጠንከር ያለ ከመሆኑ አንጻር በፓርኩ ይዞታ ላይ የሚደርሰው ጥፋት ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።  የደንና ዱር አራዊት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ አደጋው ከፍተኛ ነው፣ ከንፋሱ ጋር ተዳምሮ እሳቱ በከፍተኝ ፍጥነት እንዲዛመት አድርጎታል ሲሉ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ ከፍተኛ ነው የሚሉት ኢሳት ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ፓርኩ ህልውናው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል ይላሉ።

ቃጠሎውን ያባባሰው ንፋሱ መሆኑን የሚገልጹት ነዋሪዎች ወደ ደን ውስጥ የገባውን እሳት ለማጥፋት የማይሞከር እንደሆነ ተናግረዋል።

የደንንና ዱር አራዊት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ንፋሱና የፓርኩ ተራራማ የመልከአምድር አቀማማጥ የመከላከል ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል። የፓርኩ ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ ለእሳቱ መዛመት ምቹ ሆኗል ነው የሚሉት።

እሳቱ ወደ ገደላማው የፓርኩ ክፍል በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ በመሆኑ የፌደራል መንግስት የውጭ መንግስታትን ድጋፍ መጠየቁን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።

በፌደራል መንግስት ደረጃ አስቸኳይ ግብረሃይል ተቋቁሟል ያለው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ደቡብ አፍሪካ ስድስት ሄሊኮፕተሮችን ለመስጠት ቃል መግባቷን ገልጿል።

የእሳቱን መንስዔ በተመለከተ ምርመራ እየተደረገ ነው ከሚል መረጃ በስተቀር ትክክለኛውን ለማወቅ አልተቻለም።

ህብረተሰቡ ግን ሆን ተብሎ የተቀሰቀሰ ነው ይላል። ኢትዮጵያ በሰሜን ተራሮች ፓርክ ላይ እየደረሰ ያለውን እሳት ቃጠሎ ለማጥፋት የሌሎች ሀገራት ድጋፍን መጠየቋም ተገልጿል።