(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 30/2011) በሃገሪቱ የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋትና የዜጎችን ሰላም ለመጠበቅ ህጋዊና ተመጣጣኝ ርምጃ እንደሚወሰድ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት አስታወቀ።
የፌደራልና የክልል የፀጥታ አስከባሪ ተቋማትም አስፈላጊውን ህጋዊና ተመጣጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ መተላለፉን ምክር ቤቱ ገልጿል።
የመከላከያ ሰራዊት ግጭት በተከሰተባቸው የአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመግባት የማረጋጋት ስራ በማከናወን ላይ መሆኑንም ይፋ አድርጓል።
ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ በመላ ሃገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ የሰላም መደፍረሶችን በአጠቃላይም በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን የሰላም መደፍረስ በተለየ ትኩረት በመገምገም መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫውም በከሚሴና አጎራባች አካባቢዎች የተከሰተውን የሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት የሚወገዝ ተግባር መሆኑን አንስቷል።
በግጭቱ ህይወታቸውን ላጡ፣ አካላቸው ለጎደለና ንብረታቸው ለወደመባቸው ሁሉ ምክር ቤቱ ሀዘን እንደተሰማውም ነው የገለጸው ።
ምክር ቤቱ፥ የዜጎች በሰላም የመኖር ዋስትና እና የህግ የበላይነት ጉዳይ የመንግስት ዋነኛ የሃላፊነት ጉዳይ መሆኑን ቢጠቀስም በተግባር ግን በየአካባቢው ሞትና እልቂት መሰማቱን ቀጥሏል።
ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋትና የዜጎች ሰላም ዋስትና እንዲያገኙ የፌደራልና የክልል የፀጥታ አስከባሪ ተቋማት አስፈላጊውን ህጋዊና ተመጣጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ ብሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ብጥብጡን ያቀናበሩት፣ ያነሳሱትና የፈጸሙትን አካላት ለህግ የማቅረቡን ስራ በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰራበት መግለጫው አመልክቷል።
ለዚህም ጥናት የሚያደርግ ቡድን ከፌደራል ተቋማትና ከክልሉ መሰማራቱን ገልጿል።
የጥናት ውጤቱን መሰረት በማድረግም በብጥብጡ እጁ ያለበት ማንኛውም አካል በህግ ተጠያቂ ይደረጋልም ነው ያለው።
ምክር ቤቱ ችግሮች የሚከሰቱት የራሳቸው አጀንዳ ባላቸው የጥፋት ሃይሎች ነው ከማለት በስተቀር ጥቃቱን ማን እንዳደረሰው ከመግለጽ ተቆጥቧል።
በመደበኛም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ የህዝብ ለህዝብ ግጭት የተፈጠረ በማስመሰል የማራገብ ስራ የሚሰሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ግጭት ተከስቶ በነበረባቸው በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች በመግባት የመቆጣጠር እና የማረጋጋት ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጿል።