(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 30/2011)በቀጣዮቹ ወራት ከነዳጅና ከመድኃኒት ግዥ በዘለለ ለኢኮኖሚው የሚሆን የውጭ ምንዛሪ እንደማይኖር የብሔራዊ ባንክ ገዥው ዶክተር ይናገር ደሴ አስታወቁ።
የብሔራዊ ባንክ ገዥው ዶክተር ይናገር ደሴ የ2011 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንደገለጹት ባለፉት 8 ወራት ብቻ የ8.9 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ሚዛን ጉድለት እንደሚታይ ተረጋግጧል።
የባንኩ ገዥ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ባለፉት ስምንት ወራት አገሪቱ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ሸቀጦችና አገልግሎቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 1.64 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው።
በተጠቀሱት ወራት ከወጪ ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በ2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ9.4 በመቶ ያነሰ እንደሆነ ነው የገለጹት። ከግለሰቦችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተላከ የሐዋላ ገቢ በአጠቃላይ 3.8 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነም ዶር ይናገር አስታውቀዋል።
በተቃራኒው ባለፉት ስምንት ወራት አገሪቱ ከውጭ ለምታስገባቸው ምርቶች 10.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን፣ ይህም ወጪ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ1.3 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
በተጠቀሱት ወራት ከወጣው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ለነዳጅ ግዥ የተከፈለው 1.7 ቢሊዮን ዶላር ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝም ነው ያብራሩት።
ይባንኩ ገዥ እንዳሉት በተጠቀሱት ወራት ወደ አገር ለገቡ ሸቀጦች የተከፈለው የውጭ ምንዛሪና ወደ ውጭ ከተላኩ ሸቀጦች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ መሀል የ8.9 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ሚዛን ጉድለት ይታያል።
ጉድለቱ የተሸፈነው ታዲያ በዋናነት ከአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ፥ ከውጭ በሐዋላ ከተላከ ገቢና ከውጭ ከተገኘ ዕርዳታና ብድር መሆኑንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ያለው መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት የ2.6 ወራት ፍላጎትን ለመሸፈን ብቻ የሚበቃ እንደሆነ የብሔራዊ ባንክ ገዥው ዶክተር ይናገር ደሴ አስታውቀዋል።
እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ እየዋለ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከተለያዩ አገሮች ጋር ተነጋግረው ማምጣት የቻሉት 2.7 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጸዋል። “ይህ ካልሆነ ልናደርግ የምንችለው ያለውን የውጭ ምንዛሪ ለነዳጅና ለመድኃኒት ግዥ ብቻ በጥንቃቄ ማዋል ነው፤” ብለዋል።
የብሔራዊ ባንኩ ገዥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ያነሱት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የገባበትን አጣብቂኝ የተመለከተ ነበር።
ገዥው እንደገለጹት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2011 በጀት ዓመት እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ፣ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ 46.17 ቢሊዮን ብር ሆኖ ተመዝግቧል።
ከዚህ ውስጥም የማይመለስና አጠራጣሪ ብድሩ የአጠቃላይ ብድሩን 39.45 በመቶ እንደደረሰ ይፋ አድርገዋል። ይህም ማለት ልማት ባንክ ካበደረው አጠቃላይ ብድር ወስጥ 18.1 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ሊመለስ የማይችልና መመለሱ አጠራጣሪ ነው ብለዋል።
ይህ ብቻ አይደለም ባንኩ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት ውስጥ 344 ሚሊዮን ብር እንደከሰረ፣ ለምክር ቤቱ አስታውቀዋል፡፡