(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 17/2011)በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የእለት ደራሽ ድጋፍ ፈላጊዎች በመበራከታቸው የሀገሪቱ የመጠባበቂያ እህል ክምችት መመናመኑን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
ይህንንም ተከትሎ 6 ሚሊዮን ኩንታል እህል ከውጭ ለማስመጣት ጨረታ መውጣቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ከመጠባበቂያ እህል ክምችት በማውጣት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እርዳታና ድጋፍ ማድረግ የተለመደ ነው ።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለው የእለት ደራሽ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል።
ይህም በመሆኑ መንግስት አከማችቶት የነበረው የመጠባበቂያ እህል እየተመናመነ መምጣቱን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገልጿል።
በኮሚሽኑ የአቅርቦትና ሎጂስቲክ ዳይሬክተሩ አቶ አይደሩስ ሀሰን ለኢዜኣ እንደገለጹት በእለት ደራሽ እርዳታ ፈላጊዎች መበራከት የመጠባበቂያ ክምችቱ ተመናምኗል።
መንግስት ለመጠባበቂያ እህል ክምችቱና ለአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል እህል ለመግዛትም ጨረታ አውጥቷል ብለዋል።
ግዥው እስኪፈጸም ድረስም ለሰብዓዊ ምላሹ የሚሆን እህል ከአገር ውስጥ ዩኒየኖች ፌዴሬሽኖችና የህብረት ስራ ማህበራት፣አምራቾችና ግለሰቦች እየተገዛ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ከክምችቱ ለተለያዩ ምክንያቶች በብድር ወጥቶ የነበረውም እህል እየተመለሰ መሆኑን ነው የገለጹት።
የመጠባበቂያ እህል ክምችቱ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች እንዲሁም በሌሎች ክስተቶች ምክንያት የምግብ አቅርቦት እጥረት ሲያጋጥም ወቅታዊ ምላሽ ይሰጣል።
በአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም የእህል ገበያ ዋጋ ንረት ሲፈጠርም ገበያውን እንዲያረጋጋ የሚያግዝ ነው።
ከሰላም ሚኒስቴር በቅርቡ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሚሊዮን ዜጎች ከኑሯቸው ተፈናቅለዋል።