በጌድዮ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 17/2011)በጌድዮ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በአካባቢው የተሰማሩት የህክምና ባለሙያዎች ገለጹ።

በየወገኖቻቸውንና በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩት ተፈናቃዮች እርዳታ ለማግኘት ወደ አካባቢው በመምጣታቸው ቁጥሩ ሊጨምር መቻሉንም ገልጸዋል።

ለተፈናቃዮቹ የተለያዩ እርዳታዎች እየተደረጉ ቢሆንም ከቁጥራቸው ብዛት አንጻር ግን ለሁሉም ማዳረስ አስቸጋሪ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ተፈናቃዮቹ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ወደ መጡበት አካባቢ እንዲመለሱ ማድረግ ቢቻል ከክረምቱ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን አደጋ ለመቀነስ ይችላል ብለዋል።

በጌዲዮ ከባለፈው ሳምንት የተሻለ ነገር አለ ይላሉ በአካባቢው የተሰማሩት የህክምና ቡድን አባላት።

ዞኑ የህክምና ቡድን ማሰማራቱ፣ከአዲስ አበባ በበጎ ፈቃደኝነት የመጡ የህክምና ቡድኖች መምጣታቸው ጥሩ ጅማሮ ነው ይላሉ።

ነገር ግን የተፈናቃዮቹ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ግን ነገሩን እንዲከፋ አድርጎታል ይላሉ።የመጣውን እርዳታ ለማከፋፈል አስቸጋሪ መሆኑን በመጠቆም

የህክምና ባለሙያዎቹ ከመጪው ክረምት ጋር ተያይዞ በአካባቢው ያሉት ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውንም አስቀምጠዋል።

አሁን ላይ የመንግስት አካላት በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ እየሰበሰቡ ቢሆንም እስካሁን ግን ስራ ላይ ሲያውሉት አላየንም ብለዋል።–የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ ወደ እርምጃ እንዲገባ በማሳሰብም ጭምር።

የህክምና ባለሙያዎቹ ለተፈናቃዮቹ አሁንም ድጋፉ እንዲቀጥል የማህበራዊ ድረገጾቻቸውን በመጠቀም ድጋፍ እየጠየቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹን ወደ መጡበት ቀዬ መመለስ ምናልባትም የችግሩን ስፋት ከመቀነስ አኳያ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ሲሉም መፍትሄ ያሉትን ሃሳብ ተናግረዋል።

የህክምና ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የክረምቱ ወቅት እየቀረበ ነው ስለዚህ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ወደ ቀያቸው ተመልሰው አስቸኳይ መፍትሄ እንዲያገኙ ካልተደረገ አደጋው የከፋ ይሆናል።