(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት10/2011)በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የአምስት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።
የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እንዳስታወቀው ጥቃቱ የደረሰው በምእራብ ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ በሁምነ ዋቃዮ ቀበሌ ውስጥ ነው።
አካባቢው የኦነግ ታጣቂዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱበት መሆኑ ይታወቃል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን የተፈጸመውን ጥቃት ያደረሱት የጦር መሳሪያ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ያልታወቁ ሃይሎች ናቸው ሲል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ገልጿል።
በጥቃቱም የሁለት የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ሶስት ኢትዮጵያውያን በድምሩ አምስት ሰዎች ተገድለዋል ነው ያለው ።
ሁለቱ የውጭ ሀገር ሰዎች ዜግነታቸው ከየት እንደሆነ የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከመግለጽ ተቆጥቧል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው የሐዘን መግለጫ ግን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ በሁምነ ዋቀዮ ቀበሌ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከተቋሙ የመዳብ ማዕድን ምርመራ ፈቃድ የወሰዱ ሰን ሬይስ የተባለ ድርጅት ሰራተኞች ናቸው ብሏል።
በድርጊቱ የተሰማውን ሀዘን የገለፀው ሚኒስቴሩ፥ለተጎጂ ቤተሰቦችም መፅናናትን ተመኝቷል።
ጥቃቱን በፅኑ የሚያወግዝ መሆኑን እና አጥፊዎቹም ለህግ እንዲቀርቡ ከፍትህ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጿል።
በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን እንደሚሰጥ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታወቋል።