ፍርድ ቤቱ በእነ አቶ በረከት ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

 (ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 12/2011)የባህርዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ የ8 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

ፍርድ ቤቱ የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ በአቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ ከጠየቀው ይ14 ቀናት ጊዜ ውስጥ የ8 ቀን ተጨማሪ ብቻ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

የባህርዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት በጥረት ኮርፖሬት ዝርፊያ ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩትን አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳን ጉዳይ ተመክቷል።

የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የወንጀል መርማሪ ባለፈው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በርካታ ሰነዶችንና ሦስት በሃገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሰዎችን ማስረጃ አሰባስቦ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

ይሁንና የዳሽን ቢራ አክሲዮን ሽያጭ በተመለከተ የኦዲት ስራውን ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ጉዳዩ ውስብስብ በመሆኑ ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ አስታውቋል፡፡

የዳሽን ቢራ አክሲዮን ሽያጭ ሲፈፀም 20 የሚሆኑ ባለሙያዎች፣ውሳኔ ሰጭዎችና ከፍተኛ ሃላፊዎች የተሳተፉበት በመሆኑ የእነዚህን የቃል ምስክር ለመቀበልም የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ምርመራ ቡድኑ ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበበኩላቸው በደንበኞቻችን ላይ ተጨባጭ ማስረጃና መረጃ ሳይያዝ መታሰራቸው አግባብ አይደለም በማለት አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በችሎቱ አካባቢ የተገኙ የባህርዳር ነዋሪዎች በተጠርጣሪዎች ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር ተብሏል።