አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ለአጥፊ ጽንፈኞች አገራችንን እንዳናስረክብ ልንጠነቀቅ ይገባል ሲል አሳሰበ

 (ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 4/2011) ለዘላቂው የሚበጀንን ለዘብተኛውን መንገድ ትተን ዋልታ ለረገጡ አጥፊ ጽንፈኞች አገራችንን እንዳናስረክብ ልንጠነቀቅ ይገባል ሲል አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ አሳሰበ።

ንቅናቄው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳለው  በኢትዮጵያ የታየው የለውጥ ሂደት የፈጠረው ተስፋ  ቀስ በቀስ ጥግ በያዙ አክራሪዎችና  የቡድንን ፍላጎት ብቻ ባስቀደሙ ኃይሎች ግፊትና ጫጫታ ሊሰናከል ወደሚችል አደገኛ አቅጣጫ እየተገፋ ይገኛል።

እናም ሀገር የባሰ አደጋ ላይ ከመውደቁ በፊት ሁሉም የለውጡን ሂደት እንዲደግፍና ኢትዮጵያን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ለማድረግ በሚደረገው ጥረት እንዲሳተፍ ፣ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ አቅርቧል።

አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ 3  አይነት ኃይሎች የለውጡን ሂደት ለመቀልበስ እየሰሩ ይገኛሉ።

ይሕ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አግኝታ የነበረችውን የለውጥ እድሎች እንዳመከንናቸው ሁሉ ይህንንም የለውጥ እድል ቀልብሰን ኢትዮጵያ ልትወጣ ወደማትችለው ቀውስ ልንከታት እንችላለን ብሏል። እናም አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት አድሮብኛል ሲል ንቅናቄው አስታውቋል ።

የመንግሥት ስልጣንን በመያዝ ሲያገኙት የነበረው ጥቅም እንዳይቀርባቸው የሚሞክሩ ወይንም ለውጡ ከዚህ በፊት ለሰሯቸው በደሎች ቂም መወጫ ይሆናል ብለው የሚሰጉና በየክልሉ በተለያየ የስልጣን ደረጃ ላይ የሚገኙ ጸረ ለውጥ ኃይሎች እንዳሉም ተገንዝበናል ብሏል በመግለጫው።

በሌላ በኩል  ኢትዮጵያ የተያያዘችዉ የለውጥ ሂደት ለሁሉም ዜጎች የሚሆንና በእኩልነት የሚያይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር መሆኑን በመዘንጋት የራሳቸውን ጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት ማሟላትን ዋና አላማቸው አድርገው፤ ለዘውጌ ባለተራው የሚታደልና “ተራው የኛ ነው” በማለት “የድርሻቸውን” ለመውሰድ የቋመጡም አሉበት ነው ያለው።

ሶስተኛው አይነት አደናቃፊ ደግሞ ይህ የተያዘው የለውጥ ሂደት ያለፉት 28 አመታት ውጤት የሆነና “የለውጥ ኃይል” የሚባለውም የቀደመውን አምባገነን ሥርዓት በብልጣብልጥነት ለማስቀጠል የሚሞክር ኃይል መሆኑን ንቅናቄው ገልጿል።

አርበኞች ግንቦት 7 ባወጣው መግለጫ እንዳለው ይህ ለውጥ የታለመለትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስርቶ እንዲቋጭ ከመፈለግ ባሻገር በአሁኑ ጊዜ ምንም ሌላ አላማ የለውም።

የምንሰራው የድርጅት ሥራ ኢላማም ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርአትን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆምና የሀገሪቷን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለመ ነው ብሏል የኣአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ።

ይሕም ሆኖ ግን በሰላማዊ መንገድ በሚደረግ የሀሳብ ትግልና፤ በመጨረሻም በነጻና ፍትሀዊ ምርጫ ማህበረሰቡ የወሰነውን ውሳኔ ለመቀበል ምንም ችግር የለብንም ብሏል። ይህ እንዲሆን ግን በመጀመሪያ ሰላም እንዲሰፍን ይገባልም ነው ያለው ። ያለሰላም ፖለቲካም ዴሞክራሲም የለም ይእልው ያልው የንቅናቄው መግለጫ ያለእነዚህ ደግሞ ሀገር አይኖርም ብሏል።

የተጀመረውን የሀገር ማዳን ለውጥ መስመሩን ቢስት፣  የሚፈጠረው እጅግ አደገኛ ሀገራዊ ሁኔታ ማንም አሸናፊና ተሸናፊ የማይሆንበት አደገኛ ችግር እንደሚፈጥር አርበኞች ግንቦት 7  ጥርጥር የለኝም ብሏል።

በመግለጫው ማጠቃለያም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል፣ ድርጅት፣ ቡድንና ግለሰብ፣  የጽንፈኛ ቡድኖችና ግለሰቦች ለሚፈጥሩት ጊዚያዊ የግጭት ስሜት ሰለባ እንዳይሆን አሳስቧል።

እናም የለውጡን ሂደት በመደገፍ፣ ኢትዮጵያን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሚቻለው ሁሉ እንዲሳተፍ ፣ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ አሰተላልፏል።