በቄለም ወለጋ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች አካባቢውን ለቀው ውጡ መባላቸውን ገለጹ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 2/2011)በቄለም ወለጋ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች አካባቢውን ለቃችሁ ውጡ በሚሉ ሃይሎች እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገለጹ።

የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠ ችግሩ የሕይወት መስዋዕትነት የሚያስከፍል መሆኑንም ተናግረዋል።

ፋይል

በአካባቢው ያለው መከላከያም ሆነ የጸጥታ ሃይሉ እንዲሁም  የሚመለከታቸው አካላት ለችግሩ ምንም አይነት ምላሽ መስጠት እንዳልቻሉ ነው የተገለጸው።

በቄለም ወለጋ ዛሬ ላይ ችግር የገጠማቸው ዜጎች በ1977ቱ የሰፈራ ፕሮግራም  ከወሎ ተነስተው በቄለም ወለጋ እንዲሰፍሩ የተደረጉ የአማራ ክልል ተወላጆች ናቸው።

እነዚህ ተወላጆች ደግሞ ቁጥራቸው በሺ የሚቆጠር መሆኑንም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

ዛሬ ላይ ግን ከ30 አመት በላይ ከኖሩበት ቀዬ ለቃችሁ ካልወጣችሁ የሚል አካል መምጣቱን ይናገራሉ።

ቄሮ በሚል የተደራጀው ቡድን አካባቢው የእነሱ አለመሆኑና ወደ መጡበት መመለስ እንዳለባቸው መመሪያ አስተላልፏል ይላሉ ለኢሳት በሰጡት መረጃ ።

የተፈጠረው ችግር ደግሞ ቀላል ነው የሚባል ሳይሆን የህይወት መስዋዕትነትን የሚያስከፍል ነው ብለዋል።

ይሄን ሽሽት ወንዶቹ ወደ ጫካ መሸሽ ጀምረዋል።–ሴቶቹ ላይ የሚደርሰው የመደፈርና አካላዊ ጉዳት፣አይን ያወጣው ዝርፊያ የከፋ ሆኗል ይላሉ።

ጉዳዩ ይመለከተዋል ለሚባለው የኦሮሚያ ክልል አቤቱታቸውን ለማቅረብ ቢሞክሩም ጆሮ የሚሰጣቸው አካል አላገኙም።

ችግሩ እየተፈጠረ ያለው በሁሉም ቀበሌዎች መሆኑ ደግሞ ችግሩን የከፋ አድርጎታል ባይ ናቸው ።

በአካባቢው ያለው የመከላከያ ሰራዊትም ቢሆን አሁን ያለውን አደጋ ለመቆጣጠር አቅም የለውም ይላሉ።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ ችግሩ መፈታት ካልቻለና እኛም አይናችን እያየን ከምናልቅ ወደ መጣንበት አካባቢ መልሱን ።