የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብሔራዊ የሐዘን ቀን አወጀ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 1/2011)የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከሰከው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ለሞቱት 157 ሰዎች የዛሬው ቀን መጋቢት 2/ 2011 ዓ.ም ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲሆን አወጀ።

እናም የሪፐብሊኩ ሰንደቅ አላማ በዛሬው እለት በመላው የአገሪቱ ግዛቶች፣ በኢትዮጵያ መርከቦች ፥ በውጭ ሐገር ባሉ ኤምባሲዋችና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ዝቅ ብሎ ይውለበለባል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ የደረሰበትን አይነት ቦይንግ 737 አውሮፕላን ተጨማሪ መመሪያ እስኪስጥ ድረስ ከዛሬ ጀምሮ እንዳይበር ማገዱን አስታውቋል።

የአውሮፕላኑ አደጋ መንስኤ እየተጣራ መሆኑንም አየር መንገዱ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ 18 ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው አልፏል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳስታወቀው ትናንት ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ኬኒያ በማምራት ላይ እንዳለ ቢሾፍቱ አካባቢ ተከስክሶ የተለያዩ ዜግነት ያላቸው በአጠቃላይ 157 ሰዎች ህይወት አልፏል።

ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 302 ላይ በደረሰው አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ተሳፋሪዎች ቤተሰቦችና ወዳጆቻቸው በኢትዮጵያ መንግሥት ስም የኀዘን መግለጫ አስተላልፈዋል።

የአደጋው መንሥኤ በቴክኒክ ባለሞያዎች እየተጣራ ለሕዝብ ዝርዝር መረጃ በየወቅቱ እንደሚገለፅጽ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ  ልምድ ባለው እና በጥቅሉ ከ8000 በላይ የበረራ ሰዓት ባለው ካፒቴን ያሬድ ጌታቸው የተመራውና በረዳት አብራሪ አህመድ ኑር መሀመድ ኑር የታገዘው አውሮፕላን ወስጥ 149 መንገደኞችና 8 ሰራተኞች በአጠቃላይ የ35 ሀገራት ዜጎች ነበሩ።

አደጋው የደረሰበት የቦይንግ 737  አውሮፕላን ትናንት ጠዋት ከጆሀንስበርግ ደቡብ አፍሪካ ወደ አዲስ አበባ በሰላም የተመለሰ ነበር ተብሏል። ይህ ዘመናዊ አውሮፕላን የመጀመሪያውን የጥገና ፍተሻ እ.ኤ.አ በፌብሩዋሪ 4 ቀን 2019 አድርጎ ምንም አይነት እንከን አልተገኘበትም።

አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ኬንያ ሲበር በቢሾፍቱና በሞጆ ከተሞች መካከል ኤጀሬ በምትባል ቦታ  ነው የተከሰከሰው።

አውሮፕላን አብራሪው ካፒቴን ያሬድ ጌታቸው  ከቦሌ ኤርፖርት በተነሳ በደቂቃዎች ልዩነት ችግር እንደገጠመውና ተመልሶ ለማረፍ እንደሚፈልግ ለበረራ ተቆጣጣሪዎች አስታውቆ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያምና ሌሎች የአየር መንገዱ ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ አብራሪው በጠየቁት መሠረት ከበረራ ተቆጣጣሪዎች ፈቃድ ተሰጥቷቸው ለማረፍ ሲመለሱ ከራዳር ዕይታ ውጪ መሆናቸውና መከስከሳቸው ተገልጿል፡፡

የአደጋው ምክንያትን በሚመለከት የተጠየቁት የሥራ ኃላፊዎቹ፣ ግምታዊ ከሆነ የመላምት መልስ እንደሚቆጠቡ አስታውቀው፣ ምርመራው እስከሚጠናቀቅ መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል። ለምርመራው እገዛ የሚያደርገው ብላክ ቦክስ መገኘቱም ነው የተነገረው።

ይሕም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ የደረሰበትን አይነት ቦይንግ 737 አውሮፕላን ተጨማሪ መመሪያ እስኪስጥ ድረስ ከዛሬ ጀምሮ እንዳይበር ማገዱን አስታውቋል።

የአውሮፕላኑ አደጋ መንስኤ እየተጣራ መሆኑንም አየር መንገዱ አስታውቋል።