(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 27/2011)የአዲስ አበባ የኦሮሞ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገለጸ።
በአዲስ አበባና ኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደር የወሰን ጉዳይ እልባት ሳይሰጠው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ መተላለፋቸው ተገቢ አይደለም ሲልም ተቃውሞውን አሰምቷል።
የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ የኦሮሚያ ክልል ጥያቄ እያነሳባቸው ባሉና የክልሉን ወሰን አልፈው የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ ሂደት እንዳይተገበርም አቋም ይዟል።
በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደር የወሰን ጉዳይ አልባት እስከሚያገኝ የኦሮሚያ ክልልን ጥያቄ እያነሳባቸው ያሉ የክልሉን ወሰን አልፈው የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች በእጣ ማስተላለፍ ትክክል እንዳልሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ባወጣው መገለጫ አስታወቋል።
እናም ይህ ውሳኔ ስራ ላይ እንዳይውል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጠንካራ አቋም አለኝ ነው ያለው።
ይህ አቋም በቀዳሚነት የህዝቡን ተጠቃሚነት ላማስጠበቅ እንጂ የሀገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች አብሮ የመኖር እሴት ከመጥላት የመነጨ አለመሆኑ ከግንዛቤ ሊገባ ይገባልም ብሏል።
የክልሉ መንግስት መግለጫ እንዳለው ከአዲስ አበባ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ማናቸውም አጀንዳዎች እና ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት።
በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ተያይዘው የሚከናወኑ ስራዎች ከክልሉ መንግስትና ህዝብ እውቅና ውጪ ለመስራት መታቀዳቸው ህጋዊ ነው ብሎ እንደማያምንም አስታውቋል።
የኦሮሞ እና የኦሮሚያ መብትና ጥቅምን በማስከበር ወደተሻለ ብልፅግና ለማሸጋገር እንሰራለን በማለትም ለዚህም በህጋዊ መንገድ እንሰራለንም ብሏል።
በአዲስ አበባ ጉዳይም ከወሰንና ቤቶች ጉዳይ በዘለለ የከተማዋን የኦሮሞ ባለቤትነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል የክልሉ መንግስት መግለጫ።