አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስልጣናቸው ለቀቁ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 27/2011) አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ።

በምትካቸው ዶክተር አምባቸው መኮንን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ቃለ መሀላ ከፈጸሙ በኋላ ፖለቲካውን ከክረት በማላቀቅና ሀገሪቱን ከውጥረት በማውጣት አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት ለማድረግ የበኩሌን እወጣለሁ ብለዋል።

የአማራ ክልልን በርዕሰ መስተዳድርነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በዛሬው እለት መልቀቂያ አስገብተው ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልልን ከታኅሳስ 2006 ዓ.ም ጀምሮ በርዕሰ መስተዳድርነት መርተዋል።

ይህን ተከትሎም የክልሉ ምክር ቤት ዶክተር አምባቸው መኮንን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟቸዋል።

ዶክተር አምባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ቃለ መሀላ ከፈጸሙ በኋላ ፖለቲካውን ከክረት በማላቀቅና ሀገሪቱን ከውጥረት በማውጣት አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት ለማድረግ የበኩሌን እወጣለሁ ብለዋል።

ዛሬ በክልሉ ምክር ቤት ርእሰ መስተዳደር በመሆን የተሾሙት ዶክተር አምባቸው ቃለ መሃላ ከፈፀሙ በኋላ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ንግግር የአማራ ህዝቦችን የማስተዳደር ሀላፊነት ስለ ተሰጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

አዲሱ ርዕሰ መስተዳደር በንግግራቸው በክልሉ በቀጣይ የማስተካከያ ስራ የሚፈልጉ እንደ መንገድና መብራትን የመሰሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች ክፍተቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በመላው የክልሉ አካባቢ ሰላም እንዲሰፍን እና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት።

የስራ እድል ፈጠራን ማጎልበት እና የማምረቻ ኢንዱስትሪን ማስፋፋት እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርም ይሰራል ብለዋል።

በዚህም የክልሉን ነዋሪዎች ህይወት በቀጣይነት እንዲሻሻል በህዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎና ድጋፍ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች  በፍጥነት እና በብቃት እንዲጠናቀቁም ይሰራል ነው ያሉት።

በማህበራዊ ዘርፍ የትምህርት እና ጤና አገልግሎትን በማሻሻሉም በተለይም ደረጃቸውን ያልጠበቁ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ይደረጋል ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ ህዝቦች ወንድማማችነት መንፈስ እንዲያጎለብቱ የሚያደርግ ስራም እንደሚከናወን በርእሰ መስተዳድሩ ንግግር ተጠቁሟል።

ከትግራይ ህዝብ  ጋር የቆየውን ዘርፈ ብዙ አንድነትና ወንድማማችነት ለማደስ ለጋራ ሰላምና ብልፅግና ተግባብቶ እና ተዋዶ መስራትም የአማራ ህዝብ ፍላጎት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከምንም በላይ የምትተጠቀመው ከሰላም ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፥ አሁን ላይ የሚታዩትን ፀብ ጫሪ እና የጥላቻ ድርጊቶች ሀገሪቱንም ሆነ ዓለም የደረሰበትን የማይመጥኑ ኋላቀር እና ጎጂ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በተያያዘም የክልሉ የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባደረጉት ንግግር ባለፉት አመታት የክልሉን ህዝብ የልማት፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውሰዋል።

በሃገሪቱ ባለፉት አመታት ኪራይ ሰብሳቢነት ተንሰራፍቶ መቆየቱን ያነሱት አቶ ገዱ፥ ችግሩ የህዝቦችን አብሮ የመኖርና የጋራ እሴት በማጥፋት ሃገሪቱን ለከፋ ችግር ዳርጓት መቆየቱን አውስተዋል።

የአማራ ክልል ህዝብም ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ የዜጎች መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥባት እና ብልፅግና የተረጋገጠባት እንድትሆን ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ባንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ዛሬም የተቃውሞ ሰልፎች  በአወዳይ ከተማ “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” የሚል መፈክር መስተጋባቱ ተዘግቧል፡፡