የሕግ አስከባሪ አካላት የጦር መሣሪያ ዓይነትን የሚወሰን ሕግ ተረቀቀ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 27/2011)ከመከላከያ ሠራዊቱ ውጪ የሆኑ ሕግ አስከባሪ አካላት መታጠቅ የሚችሉትን የጦር መሣሪያ ዓይነት የሚወሰን ሕግ ተረቀቀ

ከ21 ዓመት በላይ የሆነ ጤነኛ ሰው ለግለሰብ የሚፈቀድ የጦር መሣሪያ ፈቃድ በማውጣት ሊታጠቅ ይችላል

ፋይል

በረቂቅ ሕጉ በጦር መሣሪያ ንግድና በድለላ ለሚሰማሩ ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ይሰጣል።

ከአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በስተቀር ሌሎች በክልል መንግሥታትና በፈዴራል መንግሥት የተደራጁ ሕግ አስከባሪ አካላት፣ መታጠቅ የሚችሉትን የጦር መሣሪያ ዓይነት የሚወስን ረቂቅ ሕግ ተጠናቆ ለውይይት ቀረቧል።

ረቂቅ ሕጉ የተዘጋጀው በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሲሆን፣ የሕግ ሰነዱ ተጠናቆ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።

ሪፖርተር ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ረቂቅ ሕጉ ለፀጥታ አስከባሪ አካላት የሚፈቀድ የጦር መሣሪያ ዓይነትና ብዛትን የሚደነግግ ነው።

‹‹ሕግ አስከባሪ ማለት የፌደራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ የፌደራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሲሆኑ፣ በፖሊስ አካላት የአካባቢ ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር የሚደራጁ የግል ታጣቂዎችን ይጨምራል፤›› ሲል ሕጋዊ ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡

በረቂቅ ሕጉ ተወስኖ እንዲታጠቁ የተፈቀደላቸው የጦር መሣሪያ ዓይነቶች ሽጉጥ፣ አውቶማቲክ ያልሆነ ወይም ግማሽ አውቶማቲክ የሆነ ጠብመንጃ፣ ቦምብና ሌሎች ተያያዥ ዕቃዎች ሊሆኑ እንደሚችል ረቂቅ ሕጉ ይገልጻል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሚታጠቁትን የጦር መሣሪያ ዓይነት፣ ብዛትና የአጠቃቀሙንም ሁኔታ በራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡

ይኸው ረቂቅ ሕግ ግለሰቦች የጦር መሣሪያ ለመታጠቅና ለመገልገል የሚችሉባቸውን የሕግ አግባቦችንም አካቶ ይዟል።

በዚህም መሠረት የአዕምሮ ሁኔታው የተስተካከለና አላስፈላጊ የኃይል አጠቃቀም ባህሪ የሌለው መሆኑ ሥልጣን ባለው ተቆጣጣሪ ተቋም የታመነበት ሊሆን ይገባል ተብሏል። እናም ማንኛውም ዕድሜው 21 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ  ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ፈቃድ ያለው ሰው፣ የጦር መሣሪያ የመያዝና የመገልገል ሕጋዊ ፈቃድ ሊያገኝ እንደሚችል ተመልክቷል።

በሌላ በኩል የሕግ ሥልጣን በሚሰጠው አካል መሥፈርቶችን አሟልተው ፈቃድ ማግኘት የሚችሉ አካላት የጦር መሣሪያ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ ከአገር ማስወጣት፣ ማከማቸት፣ መሸጥ፣ ከቦታ ቦታ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝ፣ ማምረት፣ ማሠልጠን ወይም መጠገን እንዲሁም በመደለል  የንግድ ሥራዎች መሳተፍ የሚችሉ መሆኑ በረቂቅ ሕጉ ተካቷል።

ረቂቅ ሕጉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረግ ውይይት ከዳበረ በኋላ የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓትን ጠብቆ ዘንድሮ  እንደሚፀድቅ ለማወቅ ተችሏል።