ልሳነ ግፉአን የህዝብና ቤት ቆጠራ መካሄዱን እቃወማለሁ አለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 27/2011)በወልቃይት፣በጠገዴ፣በጠለምት፣በራያና አካባቢው የሚደረግን ማንኛውንም አይነት የህዝብና ቤት ቆጠራ አጥብቆ እንደሚቃወም የልሳነ ግፉአን ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የህዝብና ቤት ቆጠራው እንዲራዘም ጠይቋል።

ወደዚህ ስራ ከመገባቱ በፊትም እንደሃገር የሚታዩ ችግሮችን መላው ህዝብ፣የለውጥ ሃይሉና የሚመለከታቸው አካለት ግልጽና የማያዳግም ርምጃ እንዲወስዱም ጥሪውን አቅርቧል።

ልሳነ ግፉአን ድርጅት ባወጣው መግለጫው እንደ ሃገር እየታዩ ያሉና መፍትሄ ሊቀመጥላቸው ያልቻሉ ጉዳዮችን በዝርዝር አስቀምጧል።

ባለፉት አስር ወራት የህዝብ የሰቆቃ ድምጽ ያልተሰማበት፣በሃዘን እንባ ያልፈሰሰበት የእርስ በርስ ግጭት ያልተፈጠርበትና የንጹሃን ደም ያልፈሰሰበት የሃገሪቱ ክፍል እንደሌለ በመግለጫው አስፍሯል።

ድርጅቱ እናቶች ከአራስ ቤት ሳይወጡ፣ሕጻናት ትምህርት ቤት ሔደው ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ፣አረጋውያን ከእንቅልፋቸው ሳይነቁ፣ደካሞችና ህመምተኞች የእለት መድሃኒታቸውን ማውጣት ሳይችሉ በመንግስት አፍራሽ ግብረ ሃይል ቤታቸው በላያቸው ላይ ሲፈርስባቸውና ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው አይተናል ብሏል።

የወልቃይት፣ጠገዴ፣ጠለምት ህዝብ ህወሃት ከፈጸመበት ወረራና ዘርን የማጽዳት ጥቃት ራሱን ለማዳን ወደ ጎንደርና የተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ሲሰደድ ቆይቷል።

በዚህ ብቻ ሳያበቃ ወደ ጎረቤት ሃገር ሱዳንና ወደተለያዩ የአለም ሃገራት በብዛት መሰደዱ ይታወቃል።

ይህ ባለበት ሁኔታ ውስጥ እንደ ሃገር ሊካሄድ የታሰበው የህዝብና ቤት ቆጠራ በወልቃይት፣በጠገዴ፣በጠለምት፣በራያና አካባቢው መካሄድ የለበትም ሲል ቆጥራውን አጥብቆ እንደሚቃወም ድርጅቱ አስታውቋል።

መንግስት ሊያካሂድ ያሰበው የሕዝብና ቤት ቆጥራ ጉዳይም የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ይራዘም ሲልም ጥሪውን አቅርቧል።