(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 25/2011) በብሔራዊ ቤተ መንግስት ከ300 በላይ የስልክና የኢንተርኔት መስመሮች እንዲሁም በየዓመቱ ከ11 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅም ሲውል መቆየቱን በተቋሙ አሰራር ላይ የተደረገ ጥናት አመለከተ።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በነበረው በ100 ሚሊየን ብር ሲመዘበር ቆይቷል ማለት ነው።
በምዝበራው ተሳታፊ ናቸው የተባሉ 31 ግለሰቦች ላይም እገዳ ተጥሏል።
የብሔራዊ ቤተ መንግስት የማያውቀው ከ300 በላይ የስልክና የኢንተርኔት መስመሮችን ጨምሮ ለግለሰቦች በሚውሉ መስተንግዶዎች ምክንያት በየዓመቱ ከ11 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅም ሲውል መቆየቱ ተገልጿል።
በምዝበራው ተሳታፊ ናቸው የተባሉ 31 ግለሰቦች ላይ እገዳ መጣሉ ነው የተነገረው።
ቤተ መንግስቱ አሰራሩን በአዲስ መልክ በማደራጀት ክፍተቶቹን የማስተካከል ስራ እየሰራሁ ነውም ብሏል።
በስሩ ከአስር በላይ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ቤተ መንግስቶችን የሚያስተዳድረው የብሄራዊ ቤተ መንግስት አስተዳደር በዋነኝነት ሶስት ዋና ዋና ተግባራትን ይፈጽማል።
ከቤተ መንግስት ጋር ተያይዞ የሚገኙ ቅርሶችን መጠበቅና መከባከብ፣ ትላልቅ መስተንግዶዎችን ማከናወን እና የቤተ መንግስት ግቢን በማሳደግ ራሱን በተሻለ ደረጃ እንዲያስተዳደር የሚሉ ናቸው።
የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር መቀመጫ የሆነው የብሔራዊ ቤተ መንግስት አስተዳደሩ የተሰጠውን ሃላፊነት ሲወጣ ቢቆይም ለረጅም ጊዜያት ከመመሪያና አሰራር ውጪ የሆኑ ተግባራት ሲፈጸሙበት መቆየቱን በጥናት ማረጋገጥ ተችሏል።
ባለፉት 9 ወራት በተሰራው የማጣራት ስራ ቤተ መንግስቱ በአስተዳደር ሂደት ውስጥ የሚያቀርባቸውን የመስተንግዶ አገልግሎቶች ለግለሰቦች ፍላጎት ማስፈጸሚያነት እንዲውል በማድረግ በየዓመቱ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ሲደረግ ቆይቷል።
ከስልክ፣ ኢንተርኔትና ኢ ቪድዮ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ብሄራዊ ቤተ መንግስት የማያውቃቸው ከ300 በላይ አካውንቶች በስሙ በየዓመቱ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ሲከፈል መቆየቱም ተደርሶበታል።
የገንዘቡም መጠን ሆነ የአገልግሎቱ ጉድለት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የቆየ ሲሆን፥ ይህም ወደ ገንዘብ ሲለወጥ በ100 ሚሊየን ብር የሚቆጠር ገንዘብ ሲመዘበር ቆይቷል ።
የብሄራዊ ቤተ መንግስት ችግሮቹን ከመለየት ባለፈ ድርጊት ፈጻሚዎች የሚባለኩት በአመራር ላይ የነበሩና ከአመራር የተሰናበቱ 31 ግለሰቦችን ለይቶ አግዷቸዋል።
ድርጊቱን በማስቆም ለተጠያቂነቱ ኮሚቴ በማዋቀር የማጣራት ስራን እየተከናወነ እንደሆነም የሪፖርተር ዘገባ አመልክቷል።