ጠፍቶ የነበረው የኡበር ታክሲ አሽከርካሪ ሞቶ ተገኘ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 25/2011)በቅርቡ ኡበር ታክሲ በመንዳት ላይ እያለ ጠፍቶ የነበረው ኢትዮጵያዊ ሙሰባ ባህሩ ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብሎ በሚገኝና ዴልዌር በተባለ አካባቢ ሞቶ መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ።

የ43 ዓመት እድሜ ያለው ኢትዮጵያዊ ሙሰባ ባህሩ ባለፈው ጥር ወር የኡበር ታክሲ በምሽት በመንዳት ላይ እያለ ባልታወቀ ምክንያት ተሰውሮ መቆየቱን የዋሽንግተን ዲሲ ፖሊስ አስታውቆ ነበር።

የሙሰባ ባህሩ አስከሬንን በማግኝት የተባበረው የዊል ሚንግተን ፖሊስ በኢትዮጵያዊው ሙሰባ ባህሩ አሟማት ጉዳይ ላይ ከወንጀል ጋር የተያያዘ ነገር ስለመኖሩ እስካሁን መረጋጋጫ እንደልተገኘ አስታወቋል።

ኢትዮጵያዊው ሙሰባ ባህሩ ወደ አሜሪካ የመጣው በ1998 ዓም ሲሆን ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ላለፉት 5 ዓመታት መኖሩንም ዘገባዎች አመልክተዋል።

አቶ ሙሰባ ባህሩ የሚተዳደረውም የኡበር እና ሊፍት ታክሲ በመንዳት እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።

በዴልዌር አካባቢ ሞቶ የተገኘው ኢትዮጵያዊ ሙሰባ ባህሩ ሕይወቱ ያለፈበት ሁኔታ እስካሁን ግልጽ አለመሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል።