(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 25/2011)ኢትዮጵያ በሕግ የበላይነት መለኪያ ከ126 የዐለም ሐገሮች 118ኛ ደረጃ መያዟን አንድ ጥናት አመለከተ።
በዓለም የፍትሕ ፕሮጀክት በተሠራውና በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ሰሞኑን ይፋ በተደረገው ጥናት ኢትዮጵያ ከ126 አገሮች 118ኛ ደረጃን መያዟ ታወቋል፡፡
በዓለም የፍትሕ ፕሮጀክት የተሰራው ጥናት ለሕግ ተገዥነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመለካት 120,000 የቤት ለቤትና የ3,800 ባለሙያዎችን አስተያየት መነሻ በማድረግ የዳሰሳ ጥናት አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉና በጥናቱ ከተካተቱ 30 አገራች 27ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። 20 አነስተኛ ገቢ ካላቸው አገራት ደግሞ ኢትዮጵያ 18ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጥናቱ አመልክቷል፡፡
በዚህ ጥናት መሠረት ከፍተኛ የሕግ የበላይነት ነጥብ በማስመዝገብ ዴንማርክ፣ ኖርዌይና ፊንላንድ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ኮንጎ፣ ካምቦዲያና ቬኒዝዌላ ደግሞ የመጨረሻዎቹ ሦስቱ ሃገራት ናቸው፡፡
በዓለም ሃገራት ላለፉት ሁለት ዓመታት የሕግ የበላይነት ከመሻሻል ይልቅ የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱን በጥናት ሪፖርቱ ተመልክቷል።
ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት ከፍተኛ የሕግ የበላይነት ደረጃ ያላት ናሚቢያ ስትሆን፣ ከ126 ሃገራት ሦስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
በመቀጠል ደግሞ ሞሪሽየስና ሩዋንዳ የተሻለ የህግ የበላይነት ያለባቸው ሃገራት ናቸው ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ባለ ገደብ ከ126 ሃገራት 116ኛ፣ በሙስና አለመኖር 64ኛ፣ በመንግሥት ግልጽነት 123ኛ፣ በመሠረታዊ መብቶች 124ኛ፣ በሕግ፣ሥርዓትና ደኅንነት 93ኛ፣ በሕግ ማስፈጸም 120ኛ፣ በፍትሐ ብሔር ፍትሕ 111ኛ፣ እንዲሁም በወንጀለኛ ፍትሕ 104ኛ ደረጃን መያዟ በጥናቱ መስፈሩን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡