ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተበድረው ያልመለሱ በሕግ ሊጠየቁ ነው

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 20/2011)ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተለይ ለእርሻ ሥራ ተበድረው ያልመለሱ በሕግ እንዲጠየቁ ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ።

ለእርሻ ሥራ ከልማት ባንክ ብድር ተበድረው ባልመለሱት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እየተወሰደ ያለው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሰጠው መመርያ መሠረት ነው ፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ ብድር ከ 40 በመቶ በላይ ደርሷል።ይህ የተበላሸ ብድር መጠንም ባንኩ በአስከፊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመላካች ነው።የልማት ባንክ የተበላሸ የብድር መጠን አሁን ጎልቶ ይውጣ እንጂ፣ ቀደም ባሉት ሦስትና አራት ዓመታት መጠኑ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ በ2006 ዓ.ም. የተበላሸ የብድር መጠኑ 16 በመቶ፣ በ2008 ዓ.ም. 25 በመቶ፣ በ2010 ዓ.ም. ደግሞ ወደ 40 በመቶ ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ብሔራዊ ባንክ በሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት ብድሩን ወስደው ያልመለሱ ተበዳሪዎች በሕግ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ በልማት ባንክ በኩል ተጀምሯል፡፡

ልማት ባንክ በተለይ ለእርሻ የሰጠውን ብድር ለማስመለስ ባይችል እንኳን ተበዳሪዎቹ በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ተገቢ ነው ተብሏል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥው ባለፈው ሳምንት ሰጥተውት በነበረ መግለጫ ላይ  ልማት ባንክ ለእርሻ ከሰጠው ብድር ውስጥ 6.3 ቢሊዮን ብር መመለስ የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቀው ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ሕጋዊ ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ቢገለጽም፣ ምን ዓይነት እንደሆነ ግን በግልጽ አልተነገረም፡፡

ከሁሉም የአገሪቱ ባንኮች በተለየ ሁኔታ የተበላሸ የብድር መጠኑ እየጨመረ የመጣበት ልማት ባንክ፣ ለእርሻ ብድር ወስደው ያልመለሱ ባለሀብቶችን ለሕግ ተጠያቂ ከማድረግ በተጨማሪ ራሱን እንደ አዲስ ሪፎርም እንዲያደርግም ተወስኗል፡፡

ልማት ባንክ አሁን እየተለቀቀለት ያለው ገንዘብ ውጤቱ እየተመዘነ የሚሰጥ እንጂ፣ እንደ ቀድሞ በጠየቀው ልክ እንዳልሆነ ታውቋል፡፡

ይህንን የተበላሸ የብድር መጠን ለመቀነስና ልማት ባንክ ያበደረውን የማስመለስ ሥራ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል የሚለው ጉዳይ አሁንም በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሪፖርተር ዘግቧል፡፡