በወልቃይት ዳንሻ ሁለት  ወጣቶች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 21/2011)በወልቃይት ዳንሻ ባለፉት ሁለት ቀናት በትግራይ ልዩ ሃይል በተከፈተ ጥቃት አንድ ወጣት ተገደለ፡፡

አራት ሰዎች መቁሰላቸውም ታውቋል።

በዳንሻ የአማራ ክልል ሰሌዳ ያላቸው ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይሰጡ መከልከሉን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ የትግራይ ልዩ ሃይል ከ60 በላይ ተሽከርካሪዎችን ማሰሩን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡

ትላንት የ19 ዓመት ዕድሜ ያለው ወጣት በመገደሉ የዳንሽ ነዋሪ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣቱም ታውቋል፡፡

ፋይል

ተጨማሪ ሃይል ያስገባው የትግራይ ክልላዊ መንግስት በርካታ ነዋሪዎች ማፈሱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ትላንት መከላከያ ሰራዊት ወደ ዳንሻ ቢገባም የምዕራባዊ ዞን አመራሮች ሁኔታው ከአቅማችን በላይ ባለመሆኑ መከላከያ መግባት የለበትም በማለት እንዲወጣ ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ጥቃቱ መፈጸም ከጀመረ ሁለት ቀናት ሆኖታል ነው የሚሉት ኢሳት ያነጋገራቸው፡፡

ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የአማራ ክልል ሰሌዳ ያለው ባጃጅን ጨምሮ ማንኛውም የንግድ ተሸከርካሪ መንቀሳቀስ አይችልም በሚል ገደብ መጣሉ ዳንሻን ውጥረት ውስጥ ከቷት እንደነበረ የገለጹት ነዋሪዎች ሰሌዳ በመንቀል የተጀመረው ርምጃ ወደ እስር መለወጡን ጠቅሰዋል፡፡

ሰሌዳቸውን ከተቀሙት በተጨማሪ 60 ተሽከርካሪዎች መታሰራቸውም ታውቋል።

ተሽከርካሪዎቹ የአማራ ክልል ሰሌዳ በመያዛቸው ለእስር ተዳርጉ የሚሉት ነዋሪዎች በዳንሻ በአማራ ክልል ሰሌዳ መንቀሳቀስ መከልከሉን የሚያረጋግጥ ርምጃ ነው ሲሉ ለኢሳት ተናግረዋል፡፡

በዚህ መልኩ የትግራይ ልዩ ሃይል መውሰድ የጀመረውን ርምጃ የተቃወመ አንድ አሽከርካሪ ክፉኛ መደብደቡን ተከትሎ የዳንሻ ነዋሪ በቁጣ አደባባይ መውጣቱም ተመልክቷል፡፡

በትላንትናው ዕለት የዳንሻ ነዋሪ ተቃውሞውን ማሰማት ሲጀምር ተጨማሪ ሰራዊት ያስገባው የትግራይ ልዩ ሃይል ድብደባ መፈጸሙን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመላክተው፡፡

የልዩ ሃይሉ ጥቃት በድብደባ ብቻ አለመቆሙን የሚገልጹት ነዋሪዎች በርካታ ሰዎች ታፍሰው መወሰዳቸውንም ገልጸዋል፡፡

በትላንቱ የትግራይ ልዩ ሃይል ጥቃት የበለጠ ቁጣ ውስጥ የገባው የዳንሻ ነዋሪ ተቃውሞውን በመቀጠሉ በድጋሚ ተጨማሪ ሃይል እንዲገባ መደረጉ ታውቋል፡፡

ተቃሞው በመጠናከሩ የጥይት እሩምታ የተኮሰው የትግራይ ልዩ ሃይል ሁለት ሰዎች መግደሉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ከተገደሉት በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውም ታውቋል፡፡

የተገደሉትና የቆሰሉት የዳንሻ ነዋሪዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የገለጹት ነዋሪዎች በርካታ ሰዎች ከጥቃት ለማምለጥ አከባቢውን ጥለው መሸሻቸውን ተናግረዋል፡፡

ወዴት እንደገቡ የማይታወቁ የዳንሻ ነዋሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ጥቃቱና እስሩ በዋናነት ወጣቱ ላይ ያተኮረ በመሆኑ በርካታ የዳንሻ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች ወደ አጎራባች የአማራ ክልል ከተሞች መሸሻቸው ተገልጿል፡፡

በትግራይ ልዩ ሃይል የሚወሰደው ርምጃ በመጠናከሩ ወደ ዳንሻ ከተማ የገባው የመከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን አመራሮች በኩል ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን ሁኔታው ከክልሉ መንግስት እቅም በላይ ባለመሆኑ መከላከያ ለቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

በዚህም ከዳንሻ መከላከያ ሰራዊቱ መውጣቱን ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የሚገልጹት፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ ዳንሻን ለቆ መውጣቱን ተከትሎም የትግራይ ልዩ ሀይል ተጨማሪ ወታደሮችን በማስገባት ከተማዋን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዘግይቶ በደረሰን ዜናም በትግራይ ልዩ ሃይል የተከበበው የዳንሻ ከተማ አፈሳ በስፋት እየተካሄደ ነው፡፡ ቤት ለቤት በመካሄድ ላይ ያለው እፈሳ ወጣቱ ላይ ያተኮረ መሆኑም ታውቋል፡፡

ከትግራይ ልዩ ሃይል በተጨማሪ የህወሀት የቀድሞ ታጋዮች ከሰፈሩበት ዲቪዥን በሚል ከሚታወቀው አካባቢ የታጠቁ ሃይሎች በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውንም ዘግይቶ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡

እነዚህ የቀድሞ ታጋዮች የልዩ ሃይሉን ለመርዳትና የዳንሻ ነዋሪዎችን ተቃውሞ ለማስቆም እንደሆነም ታውቋል፡፡

ጉዩን በተመለከተ ወደ አማራ ክላልዊ መንግስት ሃላፊዎች ስልክ በመደወል ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡