በወላይታ ሶዶ የፖሊስ አባላትን ጨምሮ አራት ሰዎች መሞታቸው ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 21/2011) በወላይታ ሶዶ ህገወጥ ቤቶችን ማፍረስ በሚል በተነሳ ግጭት የፖሊስ አባላትን ጨምሮ አራት ሰዎች መሞታቸው ተሰማ።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

እንደ መረጃው ከሆነም ህገወጥ ተብለው ቤታቸው የፈረሰባቸው ነዋሪዎች በጊዜያዊነት የሚያርፉበት ዳስ እንዳይጥሉ ተከልክለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ካለው ተግባር እንዲቆጠብ የወላይታ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ግንባር ማስጠንቀቂያ መስጠቱም ታውቋል።

ግንባሩ በቅርቡም ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ ማስታወቁንም መረጃዎቹ አመልክተዋል።

በወላይታ ሶዶ ባለፈው ሳምንት ህገወጥ ነው ያላቸውን 900 ቤቶች በማፍረስ የጀመረውን ዘመቻ ዛሬም አጠናክሮ መቀጠሉ ተሰምቷል።

በማፈናቀሉ ዘመቻ እስካሁን ከሁለት ሺ በላይ ሰዎች ጎዳና ላይ እንዲወድቁ ሲደረግ በቀጣይም 12ሺ ቤቶችን ለማፍረስ የተያዘው እቅድ መቀጠሉን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።