(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 19/2011) አንድ አገራዊ ፓርቲ ለመመስረት እየተደረገ ያለው ጥናት እየተጠናቀቀ ነው መሆኑን ኢህአዴግ አስታወቀ።
የዘጠኙንም ክልል ፓርቲዎችን ያካተተ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት የተወሰነው ውሳኔ በ11ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ላይ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እየተጓዘ መሆኑን የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱአለም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በበኩላቸው ከጥቂት ወራት በኋላ የአፋር፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ፣ የሶማሌ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ . ፓርቲ የሚባል ነገር የለም ማለታቸው ይታወሳል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን /በበኩሉ ጠንካራ የፖለቲካ አደረጃጀት በመፍጠር የአማራን ህልውና እውን ካደረግን በኋላ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመደራደር ወደ ዜግነት ፖለቲካ እንገባለን ብሏል።
አጋር ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር እኩል የሚሳተፉበት አንድ ሀገራዊ ፓርቲ ለመመስረት እየተደረገ ያለው ጥናት ወደ መጠናቀቂያው መድረሱን ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ገልጸዋል፡፡
አቶ ብናልፍ እንዳሉት ውሳኔው ሁሉም ዜጎች በእኩልነት በብቃታቸው እንዲሳተፉ እድል የሚፈጥር ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በበኩላቸው ሰሞኑን ከአጋር ድርጅቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ከጥቂት ወራት በኋላ የአፋር፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ፣ የሶማሌ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ ፓርቲ የሚባል ነገር የለም ማለታቸው ይታወሳል።
እንደ ዶክተር አብይ ገለጻ ኢህአዴግ ከጫፍ ጫፍ ያሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በነፃነት የሚሳተፉበት አንድ ሃገራዊ ፓርቲ ከጥቂት ወራት በኋላ ይመሰረታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጠናከር በትኩረት እሰራለሁ ብሏል።
የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ በአሶሳ ከተማ ከሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ሲወያዩ ጠንካራ የፖለቲካ አደረጃጀት በመፍጠር የአማራን ህልውና እውን ካደረግን በኋላ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመደራደር ወደ ዜግነት ፖለቲካ እንገባ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አቶ በለጠ ገለጻ አብን ወደ ብሔር ፖለቲካ ለመግባት የተገደደው ለዜግነት ፖለቲካ አሁን ያለው የፖለቲካ ምህዳር ጠባብ በመሆኑ ነው።
የዜግነት ፖለቲካ በኢትዮጵያ እንዲተገበር ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ድርጅታቸው አብን ጥረት ማድረጉን አመልክተዋል።
እናም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጎልብቶ እንዲወጣ ያለሰለሰ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።