(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 15/2011) በለገጣፎ ተፈናቅሎ ሜዳ ላይ የተጣለ አንድም ዜጋ የለም ሲሉ የለገጣፎ ከተማ ከንቲባ ገለጹ።
እስካሁንም ህገ ወጥ በሚል የፈረሰ ቤት የለም፣ የፈረሱትም በመንግስት ቦታ ላይ የተገነቡ ቤቶች ናቸው ብለዋል።
የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው ግን ክልሉ ለከተሞች ልማት ከሰጠው ትኩረት ጋር በተያያዘ በህገወጥ የተገነቡ ቤቶች እየፈረሱ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕጋዊ ከሆኑ ደግሞ መራጃ እንዲያቀርቡ አስቀድሞ ተጠይቀዋል ብለዋል።
ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው ለሚመለከተው አካል ማስረጃችንን ካቀረብን በኋላ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ቤታቸው መፍረሱን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል እስካሁን በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል የተባሉ ከ3ሺ ቤቶች በላይ መፈረሳቸውን ነው ከክልሉ ያገኘንው መረጃ ያገኘንው።
በቅርቡ በኮልፌና በኦሮሚያ ክልል መካከል በሚገኘው አካባቢ ህገወጥ ተብለው የተፈናቀሉት ከ1 ሺ በላይ ነዋሪዎች ሰሞኑን ደግሞ በለገጣፎ ሜዳ ላይ እንዲወድቁ የተደረጉትናቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች የተፈናቀሉትም ከዚሁ ከህገወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል።
የለገጣፎ ከንቲባ ወይዘሮ ሃቢባ ሲራጅ ደግሞ አንድም ዜጋ በለገጣፎ ሜዳ ላይ አልወደቀም፣ሕገ ወጥ በሚልም የፈረሱ ቤቶች የሉም ብለዋል ለኢሳት በሰጡት ምላሽ።
ቤቶቹ በሰባት ቀን እንዲፈርሱ የተደረገበት ምክንያትም አግባብነት አለው ብለዋል ወይዘሮ ሃቢባ።
የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው አቶ አድማሱ ዳምጠው ለኢሳት እንዳሉት ደግሞ በህገወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶች ፈርሰዋል። ይሄ ደግሞ ክልሉ በእቅድ ይዞት እያከናወነው ያለ ተግባር ነው።
የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው አቶ አድማሱ እንደሚሉት ከሆነ ህገወጥ ቤቶቹ ከመፍረሳቸው በፊት ማስጠንቀቂያ ተሰቷል።አማራጭ የሚሆኑ ቦታዎችም ተዘጋጅተውላቸዋል እነሱ ግን ፈቃደኛ አልሆኑም ነው ያሉት።
የተደረጉትን ጥናቶች መሰረት በማድረግ ህገወጥ ግንባታዎችን የማፍረሱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አቶ አድማሱ ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ ቤቶቹ ከመፍረሳቸው በፊት ግለሰቦቹ ህጋዊ ማስረጃዎችን እንዲያቀርቡ ጠጠይቀዋል ብለዋል።
ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው ህጋዊ ማስረጃ ብናቀርብም ቤታችን ከመፍረስ አልዳነም ይላሉ።