የኦነግ አባላት ከነበሩባቸው ቦታዎች እየተመለሱ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 15/2011) 2011በመንግሥትና በኦነግ መካከል በአባገዳዎችና በሽማግሌዎች አማካይነት የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የግንባሩ አባላት ከነበሩባቸው ቦታዎች በሰላም እየተመለሱ መሆናቸው ተነገረ።

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው የኦነግ ኃይል አዛዥ ኩምሳ ድሪባ ወይም በትግል ስሙ  መሮ በመባል የሚታወቀው ግን ይህንን ለመፈፀም ዝግጁ አይደለም ተብሏል።

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተሰማርተው የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጦር አባላት የአባገዳዎችን ጥሪ ተከትለው ትጥቅ ፈትተው ወደ ጦር ካምፖች ከመግባታቸው በፊት ወደተዘጋጁላቸው ጊዜያዊ ማቆያ ስፍራዎች እየገቡ መሆኑ ታውቋል።

ለዚሁም አባገዳዎችባ የየአካባቢዎቹ ባለስልጣናት ለውሳኔው ተገዢ  የኦነግ አባላት  ወደተዘጋጁላቸው ስፍራዎች ከነትጥቃቸው ሲመጡ አቀባበል እያደረጉላቸው መሆናቸው ነው የተነገረው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የአባገዳዎችን ጥሪ ተከትሎ ሁሉም የኦነግ ጦር አባላት እየተመለሱ አለመሆናቸው ተነግሯል።

ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው የምዕራብ ኦሮሚያ የኦነግ ጦር አዛዥ የሆነው ኩምሳ ድሪባ ወይም በትግል ስሙ መሮ የአባገዳዎችን ጥሪ አለመቀበሉ ታውቋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘው የኦነግ ጦር አዛዥ እንደሆነ በስፋት የሚነገርለት ኩምሳ ድሪባ (መሮ) ከቢቢሲ ጋር የስልክቃለምልልስ ማድረጉ ነው የተነገረው።

በዚሁቃለምልልስም መሮ ባለው ሁኔታ ስምምነቱን ተቀብሎ ለመግባት ዝግጁ እንዳልሆነ ገልጿል።

የአባገዳዎችን ጥሪ ለመቀበል እና እርቅ ለማውረድ ዝግጁ ስለመሆኑ ተጠይቆ “የእርቅ  ኮሚቴው  አባላት እኔን በአካል አግኝተው ለማነጋገር ፍላጎት የላቸውም ብሏል።

ትኩረት ያደረጉት ጦሩን አንድ በአንድ እጁን እንዲሰጥ ማድረግ ላይ ነው” በማለት እሱም እነሱን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱንም ነው የገለጸው።

እንዲያውም “ጦሩን የመበታተን ዓላማ ይዘው ነው እየተንቀሳቀሱ ነው ሲል የእርቅ ኮሚቴ አባላትን ወቅሷል።

“ወደፊት መራራ ትግል ማድረጋችንን እንቀጥላለን” ያለው መሮ “ብቻዬን ብቀር እንኳ ትግል ማድረጌን እቀጥላለሁ እቅዴም ይሄው ነው” በማለት በትጥቅ ትግሉ እንደሚቀጥል ገልጿል።

በተያያዘ ዜናም የኦነግ አባላት ትጥቅ ፈተው በሰላማዊ መንገድ ወደ ካምፕ እንዲገቡ ለማድረግ ወደ አካባቢው የተጓዙት አባገዳዎች መታገታቸው ተሰምቷል።

ከአባገዳዎቹ መካከልም ድብደባ የተፈጸመባቸው መኖሩም ነው የታወቀው።

ቁጥራቸው በውል ያልታወቀውና ታግተዋል የተባሉት አባገዳዎች ይሄ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የታወቀ ነገር የለም።