(ኢሳት ዲሲ–የካቲት/2011) አስር የቀድሞ መርማሪዎች አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል የሚል ክስ ቀረበባቸው።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስሩ የቀድሞ መርማሪዎች በአጠቃላይ 78 ክሶች እንደተመሰረተባቸው አስታውቋል።
ከክሶቹ መካከል እስረኞችን እጃቸውን በካቴና በማሰር፣ በጣት እንዲቆሙ በማድረግ፣ በኤሌትሪክ ገመድ በመግረፍና በግንባር ግድግዳ በማስገፋት እና በኤሌክትሪክ በማስነዘር ይርገኝበታል።
በብልታቸው ላይ 2 እስከ 4 ሊትር ሃይላንድ ውኃ በማንጠልጠል ከ2 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት እንዲቆዩ በማስደረግ፣ ፣ ብልታቸውን በፒንሳ በመሳብ የጭንቀት ህመም እና ተያያዥ ድብርት እንዲደርስባቸው አድርገዋል የሚሉትም ከኽሶች መካከል ናቸው።
አስሩ ተከሳሽ መርማሪዎች «በቀዝቃዛና ጨለማ እስር ቤት ውስጥ በማሰር፣ በእግራቸው መሀል እንጨት አስገብቶ በመገልበጥ የውስጥ እግራቸውን በኤሌትሪክ ገመድ በመግረፍ፣ በምርመራ ክፍሉ በተዘጋጀ ሚስማር ላይ በማንጠልጠል ለረዥም ሰዓት እንዲቆዩ በማድረግ ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ፈጽመዋል
ከዚህ በተጨማሪም አድካሚ እና ከባድ ስፖርት በማሰራት፤ አፍንጫ ውስጥ እስክሪብቶ በመክተት፣ መቀመጫቸውን እና ጀርባቸውን ውኃ እየደፉ በኤሌክትሪክ ሽቦ በመግረፍ፣ ጺማቸውን በመንጨት ፣ብልታቸውን በቀጭን ሲባጎ በማሰር በግል ተበዳዮች ላይ ሞራላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት አስከትለዋል» ብሏል የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ።
አስሩ ተከሳሾች ኮማንደር ዓለማየሁ ኃይሉ፣ ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፋይኔ ወልደ ሚካኤል፣ ዋና ሳጅን ኪዳኔ አሰፋ ሸማ፤ ዋና ሳጅን ርዕሶም ክህሽን፣ ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜ በዳዳ፣ ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሐሰን መኮንን፣ ምክትል ኢንስፔክተር ምንላርግልህ ጥላሁን፣ ረዳት ኢንስፔክተር መንግሥቱ ታደሰ አየለ፣ ረዳት ኢንስፔክተር ኃይሉ ሁንዴ እና ኢንስፔክተር ስንታየሁ ፈጠነ ለገሰ ናቸው።
ተከሳሾች በፌድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 12ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ክስ መቀበላቸውን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል። በመጪው የካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ክሱ በችሎት የሚነበብ ሲሆን በተከሳሾች የዋስትና መብት ላይ ክርክር እንደሚደረግ ዘገባዎች አመልክተዋል።