የኢትዮጵያ አየር ሃይል ጥቃት ማድረሱ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 22/2011)የኢትዮጵያ አየር ሃይል በሶማሊያ የአልሻባብ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ማድረሱን ገለጸ።

44 ደቂቃ በዘለቀው ጥቃት የአልሻባብ አመራሮችን ጨምሮ 35 የአልሻባብ ታጣቂዎች መገደላቸውንም የኢትዮጵያ አየር ሃይል ለመንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን አስታውቋል።

ከሶማሊያ ባይድዋ ግዛት በስተምስራቅ 75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቡርሃይቤ በተባለው የአልሻባብ ይዞታ ላይ ጥቃቱ መሰንዘሩንም መረዳት ተችሏል።

ባላፈው ሳምንት መጨረሻ ጥር 16/2011 የኢትዮጵያ አየር ሃይል ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች በፈጸሙት ጥቃት በስፍራው የአልሻባብ የኦፕሬሽን ሃላፊ የነበረው አብዱ ኡስማንና የፈንጂ ቡድን ሃላፊው አብዱሰላም መገደላቸውንም የኢትዮጵያ አየር ሃይል አስታውቋል።

በጥቃቱ በአጠቃላይ 35 የአልሻባብ ታጣቂዎች ሲገደሉ 5 ተሽከርካሪዎች መውደማቸውም ተመልክቷል።

ከወደሙት 5 ተሽከርካሪዎች አንዱ ፈንጅ የጫነ ነበር ያለው የኢትዮጵያ አየር ሃይል 5 ካሊበር መሳሪያዎችም እንደወደሙ አስታውቋል።

የሶማሊያው ነውጠኛ ሃይል አልሻባብ ከሳምንት በፊት በሶማሊያ በሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን መንግስት አምኖ ነበር።