በቴፒ ግጭት ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 23/2011) በቴፒ ጋብ ብሎ የነበረው ቀውስ ዳግም ማገርሸቱ ተሰማ።

የሰው ህይወት የጥፋበት ግጭት ዛሬ መቀስቀሱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በኮንሶ ከአስተዳደር መዋቅር ጋር የተያያዘው ውጥረትም ሰሞኑን መባባሱን ለማወቅ ተችሏል።

ለውጥ አደናቃፊ የሆኑ የደቡብ ክልል አንዳንድ ባለስልጣናት አካባቢው እንዳይረጋጋ እያደረጉ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ይከሳሉ።

በሌላ በኩል የክርስትና እምነት ተከታይ በሆኑ የጅጅጋ ነዋሪዎች ላይ ሰሞኑን ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ጊዜያዊ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉ ተገልጿል።

ህዝባዊ ትዕይንቶችና ስብሰባዎችም በጊዜያዊነት መታገዳቸውን የደርሰን መረጃ ያመለክታል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ወደ ሰነበተችበት ቀውስ ተመልሳ ገብታለች።

ያዝ ለቀቅ ሲያደርገው የነበረው ግጭት ዛሬ አገርሽቶ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በከተማዋ ነዋሪና በሸካ ማህበረሰብ ተወላጆች መካከል ተፈጥሯል የተባለው ግጭት ባለፉት ሁለት ወራት መለስተኛ መሻሻል አሳይቷል ቢባልም ዛሬ በተፈጠረ ግጭት ውጥረት መከሰቱን ለማወቅ ተችሏል።

በሸካ ተወላጆች ጥቃት ደረሰብን ያሉ የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች ራሳችንን ለመከላከል በሚል መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሞ ማድረጋቸውን ተከትሎ የጸጥታ ሃይሎች ርምጃ መውሰዳቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

በተለይም በቴፒ ከተማ መናሃሪና ባጃጅ ተራ በሚል በሚጠሩት ሰፈሮች ግጭቱ የከረረ መሆኑን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች ነዋሪው በድንጋይና በተቃጠሉ ጎማዎች መንገዶችን ዘግቶ መዋሉ ታውቋል።

እስከአሁን ባለው መረጃ አምስት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች ግጭቱ ወደለየት የህዝብ እልቂት ከመቀየሩ በፊት የፌደራል መንግስት በአስቸኳይ ጣልቃ መግባት አለበት ሲሉ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በኮንሶ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እየተባባሰ መምጣቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ኮንሶ የዞን መዋቅር ይገባታል በሚል የተጀመረው ተቃውሞ በክልሉ ልዩ ሃይልና በመከላከያ ሰራዊት በተወሰደ የሃይል ርምጃ ወደከፋ ደረጃ ሊለወጥ እንደቻለም ይነገራል።

ኢሳት ያነጋገራቸው የኮንሶ ነዋሪዎች እንደሚሉት የህዝቡን ጥያቄ በሃይል ለማፈን የደቡብ ክልል የለውጥ አደናቃፊ የሆኑ ባለስልጣናት ችግሩን አባብሰውታል ሲሉ ይከሳሉ።

ባለፈው ሰኞ ለኢሳት ቃለመጠይቅ የሰጡት የደቡብ ክልል የሰላምና ደህነት ቢሮ ሃላፊ አቶ ወንድሙ ገብሬ ችግሩን ለመፍተታ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።

በኮንሶ ተቃውሞ የተገደሉ ሰዎች መኖራቸውም ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ተከስቶ የነበረውን ችግር ለማስቆም የክልሉ መንግስት የሰአት እላፊ አዋጅ መደንገጉ ተገልጿል።

የክርስትና እምነት ተከታይ በሆኑ የጅጅጋ ነዋሪዎች ላይ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ያደራጃቸው ሄጎ በሚል የሚጠሩት ወጣቶች የሰነዘሩትን ጥቃት ተከትሎ የክልሉ ልዩ ሃይል ተኩስ ከፍቶ አራት ሰዎችን መግደሉ የሚታወስ ነው።

የክልሉ መንግስት ሁኔታውን ለመቆጣጠር እንዲያስችለው የሰአት እላፊ ገደብ የጣለ ሲሆን ማንኛውንም ስብሰባና የአደባባይ ትዕይንቶችንም በጊዜያዊነት ማገዱን አስታወቋል።

ገደቡ እስከመቼ እንደሚዘልቅ የክልሉ ደህንነትና ጸጥታ ቢሮ የሰጠው መረጃ የለም።