(ኢሳት ዲሲ–ጥር 22/2011)የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ባለፈው ሰኔና ሐምሌ በክልሉ ግጭት እንዲነሳ በማድረግ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል ዛሬ ክስ ተመሰረተባቸው።
እንዲሁም ሴቶች እንዲደፈሩና ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ፣ በሃይማኖት ተቋማት ላይም ጥቃት እንዲፈጸም ማድረጋቸውንም አቃቤ ሕግ ገልጿል።
ከወራት በፊት በቁጥጥር ስር ውለው በአዲስ አበባ ወህኒ ቤት የሚገኙት አቶ አብዲ መሐመድ ክስ የተመሰረተባቸው ከሌሎች 46 ግለሰቦች ጋር መሆኑን ነው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ያስታወቀው።
በጦር መሳሪያ የታገዘ አመጽ እንዲካሄድ በማድረግ፣የእርስ በርስ ግጭት ለመቀስቀስ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉት አቶ አብዲ መሐመድ ኢሌና የ46ቱ አባሪዎቻቸው ጠበቆች ዛሬ ፍርድ ቤት ባለመገኘታቸው ክሱን ለመስማት ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱም ታውቋል።
የዛሬ ሳምንት ረቡዕ ጥር 29/2011 ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ለተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ በጽሑፍ እንደደረሳቸው ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።
የተከሳሾቹ ክስ በሁለት ተከፍሎ የቀረበ ሲሆን ከ1ኛ እስከ 26ኛ ያሉት ተከሳሾች በሰኔና በሐምሌ ወር 2010 ሔጎ በሚል ወጣቶችን በማደራጀት የሶማሌ ብሔር ተወላጅ ባልሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ንብረታቸውን ለመዝረፍና ለማውደም መንቀሳቀሳቸውን በዚህም የሰው ሕይወትና ንብረት መውደሙ ተዘርዝሯል።
በክሱ ውስጥ ከተዘረዘሩት 47 ተከሳሾች ከተራ ቁጥር 27 እስከ 47 የተመለከቱት ደግሞ ከሐምሌ 28 እስከ ሐምሌ 30/2010 በተመሳሳይ ወጣቶችን በማደራጀትና በማስታጠቅ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ክስ እንደተመሰረተባቸውም ታውቋል።
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ በ59 ሰዎች ሕይወትና በ412 ሚሊየን ብር ንብረት ውድመት ተጠያቂ ሆነዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በትላንትናው እለት ሃይማኖታዊ በአል አክብረው በሚመለሱ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ ጅጅጋ ከተማ ውስጥ የተደራጁ ወጣቶች በሰነዘሩት የድንጋይ ጥቃት ግጭት መፈጠሩንና የሰው ሕይወት ማለፉም ታውቋል።