የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መዳረሻውን ሊያሰፋ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 22/2011)የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሰሜን አሜሪካ የበረራ መዳረሻውን ሊያሰፋ መሆኑን አስታወቀ።

አየር መንገዱ ወደ ሒውስተን አዲስ በረራ በመጀመር ወደ አፍሪካ የሚበሩትን መንገደኞች ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ መስመር እንደሚዘረጋም ታውቋል።

ከኢትዮጵያ በየቀኑ በመብረር በሳምንት 7 ጊዜ ወደ ዋሽንግተን የሚያደርገውን ምልልስም 3 በረራዎችን በመጨመር ወደ 10 ማሳደጉንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደገለጹት ተቋማቸው በሰሜን አሜሪካ የሚያደርገውን በረራ በአዲስ መልክ እያደራጀ ነው።

ይህ አደረጃጀት መንገደኞች የተሻለ አገልግሎትና አቋራጭ መዳረሻ እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው ብለዋል።

በአሜሪካ የበርካታ የአፍሪካ ሃገራት የማህበረሰብ አባላት የሚገኙ በመሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚሁ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን አቶ ተወልደ ገልጸዋል።

እናም ከኢትዮጵያ ወደ ሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በየቀኑ ይደረግ የነበረው በሳምንት የ7 ጊዜ በረራንም ወደ 10 ማሳደጉን ነው የገለጹት።

ከዚህ ቀደም ወደ ካሊፎርኒያ የነበረው የቀጥታ በረራ እንዳለ ሆኖ ወደ ሂውስተን ቴክሳስ አዲስ መስመር መዘርጋቱንም ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ተወልደ ገለጻ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 አየር መንገዱ መዳረሻውን በማስፋት የሰሜን አሜሪካ ገበያን ለመቆጣጠር እየሰራ ይገኛል።

በቅርቡ ደረጃውን የጠበቀ የደንበኞች ማስተናገጃ ተርሚናልን በማስፋፋት ያስመረቀው አየር መንገዱ ዘመናዊ ሆቴል በማሰራትም አገግሎቱን እያሰፋ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።

ተርሚናሉ ከ250 ሚሊየን ዶላር በላይ የፈሰሰበት ሲሆን ስካይ ላይን የተባለው ዘመናዊ ሆቴል ደግሞ ከ54 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጭ ተደርጎበታል።