ታህሳስ 26 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ የሚገኙ ባንኮች ደንበኞቻቸው ከ200 ሺ ወይም ከ10 ሺ ዶላር በላይ ገንዘብ ሲያስገቡም ሆነ ሲያስወጡ ለብሄራዊ የጸረ ሽብር የመረጃ ማእከል ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘዙ
የጸረ ሽብር የመረጃ መእከል ለግልና ለመንግስት ባንኮች ባወረደው መመሪያ ማንኛውም ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ አገር ዜጋ ከ200 ሺ ብር ጀምሮ በባንኮች ለማስቀመጥ ወይም ለማውጣት በሚሄድበት ጊዜ፣ ባንኮች የግለሰቦችን ስምና ማንነት ለብሄራዊ የጸረ ሽብር የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማእከል ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የጸረ ሽብር ግብረሀይሉ ይህን ትእዛዝ ያስተላለፈው፣ በአገር ውስጥ የሚደረግን የጸረ ሽብር እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ነው በሚል ምክንያት ነው።
መመሪያው ከጥር 1 ጀምሮ ተግባራዊ የሚመሆን ሲሆን፣ መመሪያውን በማይፈጽሙ ባንኮች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተብሎአል።
መንግስት ከዚህ ቀደም ባወጣው መመሪያ ከ10 ሺ ዶላር በላይ ለማስቀመጥ ወይም ለማውጣት ወደ ባንኮች የሚሄዱ ግለሰቦችን ማንነት ራሳቸው ባንኮች እንዲያጣሩ ያደርግ ነበር።
ይሁን እንጅ መንግስት በአገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ አየር አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ፣ አንድ ዜጋ በአንድ ጊዜ ወይም በተከታታይ ቀናት ወይም ወራት በድምሩ እስከ 200 ሺ ብር የሚደርስ ገንዘብ ከባንክ ካወጣ ወይም ወደ ባንክ ካስገባ፣ ባንኮች የግለሰቡን ማንነት ለጸረ ሽብር ግብረሀይሉ መላክ ይጠበቅባቸዋል።
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የባንክ ሰራተኛ እንዳሉት ውሳኔው በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ላሉ የፖለቲካ ሀይሎች የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉ ለመከላከል ነው።
መንግስት በቅርቡ አኬልዳማ በሚል ርእስ በሰራው ድራማ ላይ በውጭ የሚገኙ ሀይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ለማስነሳት ከ500 ሺ ብር በላይ መድበዋል በማለት መግለጡ ይታወሳል።
አዲሱ መመሪያ የግለሰቦችን የገንዘብ ሚስጢር ለመንግስት ባለስልጣናት አሳልፎ የሚሰጥ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ባንኮች የሚጠቀሙ ዜጎች ችግር ይገጥማቸዋል ተብሎ ተፈርቷል።
መንግስት ማን ምን ያክል ገንዘብ በእየቀኑ እንደሚያንቀሳቀስ በሚደርሰው መረጃ መሰረት የመንግስት ደጋፊ ያልሆኑ ወይም በተቃዋሚነት የተፈረጁ ግለሰቦች ገንዘባቸው ለሽብርተኝነት ማስፈጸሚያ ይውላል በሚል ሰበብ ሊነጠቁ እንደሚችሉ ባለሙያው ያክላሉ።