ኢቲቪ ‘‘አኬልዳማ’’ በሚል ርዕስ ያስተላለፈው ፕሮፓጋንዳ የተሰራው መንግስት እልክ በመጋባቱ መሆኑን አቶ በረከት ስምኦን ጠቆሙ

ታህሳስ 26 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በቅርቡ ‘‘አኬልዳማ’’ በሚል ርዕስ ያስተላለፈው ፕሮፓጋንዳ  እንዲሰራ የተወሰነው፤ መንግስት  ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከፕሬሶች  ጋር እልክ በመጋባቱ  መሆኑን አቶ በረከት ስምኦን ጠቆሙ።

አብዛኛው ህዝብ-ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዓመታዊ ግብር  አልከፍልም ማለቱንም ተናገሩ።

ለዝርዝሩ ደረጀ ሀብተወልድ፦

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ በረከት ስምኦን  ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት  ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ፤መንግስት የሽብር ተጠርጣሪዎችን ከፍ/ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ካወጣ በኋላ በቁጥጥር ሥር አውሎ፣ ማስረጃዎቹን ይዞ ወደ ፍ/ቤት ሄዷል ብለዋል።

ነገር ግን  እርሳቸው እንዳሉት፤ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ንክኪ አላቸው ያሏቸው ፓርቲዎች- ፕሬሶችን በስፋት በመጠቀም፤ መንግስት አለአግባብ እሥር እየፈፀመ መሆኑን በመጥቀስ” ሰዎቹ ነፃ ናቸው” በሚል ብይን መስጠት በመጀመራቸው፤ በኀብረተሰቡ ውስጥ ‘‘ሰዎቹ ለምን ታሰሩ?’’ የሚል ጥያቄ  ተፈጠረ ።

በዚህም ሳቢያ  የህዝቡን ጥያቄና ቅሬታ ለማለዘብ ሲባል-ወይም እርሳቸው እንዳሉት ህዝቡን ለማስረዳት በሚል   መንግስት “አኬልዳማን” ለመስራት ተገደደ።

‘‘የተካሄደው ዘመቻ ተጠርጣሪዎቹ ወንጀል ፈፅመዋል ወይም አልፈፀሙም በሚል ብቻም የሚወሰን ሳይሆን፤ መንግስት ሰዎቹን ማሰር የፈለገው; ሰውን ለማስፈራራትና ኀብረተሰቡን ለማሸበር ስለፈለገ ነው የሚል ሰፊ ዘመቻ በመካሄዱ -መንግስት  ይህ አለመሆኑን ለማሳዬት አኬልዳማን ለመስራት ተገዷል”ብለዋል- አቶ በረከት ስምኦን።

አያይዘውም በአኬልዳማ ፕሮግራም ላይ ብይን እንዳልተሰጠ፣ ብይን የመስጠት ሥራ የፍ/ቤት መሆኑን፣ ይህንኑ ጉዳይም ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ተጠይቀው ማብራሪያ መሰጠታቸውን ተናግረዋል።

ይሁንና አቶ መለስ በፓርላማ ቀርበው፦”የታሰሩት በሙሉ ወንጀለኞች ናቸው። ለሁሉም ከበቂ በላይ መረጃ አለን” በማለት  በአደባባይ ስለሰጡት ፍርድ -አቶ በረከት ያሉት ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ደርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም በበኩላቸው ድርጅቱ አኬልዳማ የተሰኘውን ፕሮግራም  ከሰራ በኋላ  በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል ክስ እንደቀረበባቸው ለም/ቤቱ ተናግረዋል።

‘‘ ለተወካዮች ም/ቤት  የክስ ደብዳቤ ተፅፎ ግልባጩ ለኤምባሲዎች ነው የተላከው። የአንድ አገር ሉዐላዊነት የሚጥስ ክስ ነው የቀረበብን’’ ብለዋል-አቶ ዘርዓይ።
ፕሮግራሙን  ከማዘጋጀታቸው በፊትም የሕግ ባለሙያ ማማከራቸውን የጠቀሱት አቶ ዘርዓይ፤ ከፕሮግራሙ ጋር በተያያዘ በፍ/ቤት ክስ ቀርቦባቸው ፍ/ቤቱ ውድቅ እንዳደረገውም ገልፀዋል።
በፓርላማው ብጨኛው የአንድነት ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ግን  ሪፖርቱን አጣጥለውታል።

“ በአኬልዳማ ዘጋቢ ፊልም እገሌ 10 ወይም 15 ዓመት ይቀጣ ባይባልም፤ ስሙ እየተጠራ ‘‘አሸባሪ’’ ተብሏል። ‘‘እኔ እዚህ ም/ቤት ውስጥ ቁጭ ብዬ የተናገርኩት ንግግር ምስሌ እዚያ ውስጥ ገብቶ አሸባሪ ናቸው ከተባሉት ጋር ቀርቧል። እኔ እዚህ ቁጭ ያልኩት ለአሸባሪነት አይደለም። አንድነት የአሸባሪ ድርጅት አይደለም። ይሄ ስም ማጥፋት ነው’’ ብለዋል-አቶ ግርማ።

አያይዘውም ይህንኑ ቅሬታቸውን በአድራሻ ለኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና ለኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለስልጣን ፤ ለሚመለከታቸው አካላት ደግሞ በግልባጭ በደብዳቤ ፓርቲያቸው ማሳወቁን የጠቀሱት አቶ ግርማ፤ የብሮድካስት ባለስልጣን “በድርጅቱ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ መሠረት አስተናግዷቸው” ቢልም፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሊያስተናግዳቸው አለመቻሉን ገልጸዋል።

አቶ ግርማ አያይዘውም፦ ‘‘እኛ በምንከፍለው ግብርና ታክስ ጭምር ነው ደመወዝ የሚከፈላችሁ። ኀሳባችን መደመጥ ነበረበት። ሌላው ቀርቶ በምንድነው ቅር የተሰኛችሁት ብሎ የጠየቀን የለም’’ ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።
አኬልዳማ ሲሰራ የሕግ አማካሪ አማክረናል የተባለው እንዳልተዋጠላቸው የተናገሩት አቶ ግርማ፤ በፍ/ቤት ተከስሰን ነበር የተባለውም  የአቶ ዘርዓይ ቅሬታ ስህተት እንደሆነ አመልከተዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በቴሌቪዥን ስማችን ጠፍቷል፣ በፍ/ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ ዘገባ መተላለፉ ተፅዕኖ ያሳርፋል በማለት ለፍ/ቤቱ አቤቱታ ከማቅረባቸው ውጪ በፓርቲው የቀረበ ክስ እንደሌለ አስረድተዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ከቴሌቪዥን ባለቤትነት ፈቃድ በዓመት 50 ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ቢንቀሳቀስም ፤ውጤቱ ደካማ መሆኑን አቶ በረከት በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ በረከት ገለፃ፤በገቢ አሰባሰቡ ላይ ከቴሌቪዥን ባለቤትነት ፈቃድ ክፍያ የተሰበሰበው ገቢ ለመሰብሰብ ከታቀደው ጋር ሲነፃፀር፤ 26 በመቶ ያህል ብቻ ነው።’’
ለዚህ ገቢ ማነስ ምክንያቱ የሕዝቡ ለመክፈል ያለው ዝግጁነትና ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን አንዱ ነው ያሉት አቶ በረከት ድርጅቱም ቢሆን ሕዝቡን በመቀስቀስና በማነሳሳት እንዲከፍል ለማድረግ የሰራው ሥራ ደካማ መሆን ተጨማሪ ምክንያት ነው ብለዋል።

የድርጅቱ  ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ችግር እንዳለ አልሸሸጉም ‘‘በዓለም አቀፍ ደረጃ አነሰተኛ ክፍያ የምትጠይቅ አገር ኢትዮጵያ ናት። በቀን የምናስከፍለው 15 ሳንቲም ነው። ብዙ ሰዎች ለአንድ ፊልም ብቻ  30 እና 40 ብር እንደሚከፍሉ እናውቃለን። በኬንያ እና በጅቡቲ ክፍያው በብዙ ዶላር ነው’’ ብለዋል።

ኬንያ የግሎችን ጨምሮ መንግስትን አጠንክረው  የሚተቹና የሚነቅፉ በትንሹ ከ 34 በላይ ልዬ ልዩ ቻነሎች  በነፃነት የሚተላለፉባት አገር መሆኗን ያስታወሱ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፤ አቶ ዘርዓይ፤የሚመሩትንና 82 ሚሊየን ህዝብ የ አንድን ጠባብ ቡድን ቀኖና ብቻ እንዲሰማ የተገደደባትን አገር  የቴሌቪዥን ጣቢያ- ከኬንያ ጋር ለማነፃፀር መሞከራቸው አስቂኝ ነው ብለዋል።

ህዝቡ በዚህችውም አንዲት ጣቢያ በነጋ በጠባ የሚለፈፈው ውሸት ብቻ እንደሆነ ከተረዳ ውሎ አድሯል ያሉት እኚሁ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፤ ለውሸት  ዋጋ እስከሌለው ድረስ ህዝቡ የቴሌቪዥን ግብር አልከፍልም ማለቱ የሚደንቅ አይደለም ብለዋል።

አብዣኛው ህዝብ ዲሽ በማስገባት ዓረብ ሳትንና ሎሎች ጣቢያዎችን ወደመከታተል ለመሄድ በመገደዱ  ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተመልካች ድርቀት እንደተመታ መረጃዎች ያሳያሉ።

ዲሽ ለማስገባት አቅማቸው ባለመቻሉ አልፎ አልፎም ቢሆን ኢቲቪን ለማየት የተገደዱትና  ”ዲሺ የሌላችሁ፤እንደምን አመሻችሁ” የተባለላቸው ወገኖች ደግሞ  እንኳን ግብር ሊከፍሉ ቀርቶ- እኛ ላየንበት ኢቲቪ ሊከፍለን ይገባል በማለት  በተደጋጋሚ በኢቲቪ  ፕሮፓጋንዳ መማረራቸውን ሲገልጹ ይደመጣሉ።