(ኢሳት ዲሲ–ጥር 15/2011)በኢትዮጵያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መደረጉንና ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሲዊዘርላንድ ዳቮስ በሚካሄደው የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ዛሬ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የዲሞክራሲ ምህዳሩ መስፋቱን በዚህም የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩና በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ወደ ሃገር ቤት ተመልሰው ሰላማዊ ትግል መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለማሻሻል የግል ዘርፉን ማስፋት የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን በንግግራቸው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የወጣቶችና የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ከ48 አመት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1971 የተቋቋመውና መቀመጫውን በኮሎኝ ስዊዘርላንድ ያደረገው የአለም ኢኮኖሚ ፎረም አመታዊ ሽያጫቸው ከ5 ቢሊየን ዶላር በላይ የሆነ 1ሺ ያህል ኩባንያዎች በአባልነት የሚሳታፉበት መድረክ ነው።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2020 የኢኮኖሚክ ፎረምን ልታዘጋጅ መሆኗም ታውቋል።