(ኢሳት ዲሲ–ጥር 6/2011) በቅማንትና በአማራ ህዝብ መካከል በተፈጠረ ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ።
ባለፉት ሁለት ቀናት ሽንፋ በተባለ የመተማ ወረዳ አካባቢ ሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ ሰብዓዊ ጥፋት ካደረሰ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ለኢሳት ገልጸዋል።
ሃላፊው አቶ አሰማህኝ አስረስ የሁለቱ ወገኖች ግጭት በሶስተኛ ወገን የተጠነሰሰና እንዲባባስ የሚደረግ ነው ብለዋል።
ይህን በስም ያልጠቀሱትን ሶስተኛ ወገን እጁን ክልሉን ከማተራመስ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል።
የቅማንትና የአማራ ህዝቦችም የዘመናት አብሮነታቸውን በደም እንዳይጨቀይ የሚችሉትን ትዕግስት በመውስድ ራሳቸውን ለሌላ ወገን መጠቀሚያ ከማድረግ እንዲርቁ ጥሪ አድርገዋል።
በቅማንትና አማራ ህዝብ መካከል የተፈጠረው ግጭት የሁለቱም ወገኖች ፍላጎት ባለመሆኑ እጁን ያስገባው አካል ከድርጊቱ እንዲቆጠብ የአማራ ክልል መንግስት አስታወቋል።
የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ አሰማህኝ አስረስ ለኢሳት እንደገለጹት የቅማንትና የአማራ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ያልነበረ ቅራኔ በመፍጠር፣ በመሳሪያና በገንዘብ በመደገፍ ግጭቱ የከፋ መልክ እንዲይዝ ያደረገው አካል በአስቸኳይ እጁን ሊሰበስብ ይገባል ብለዋል።
አቶ አሰማህኝ እጁን አስገብቷል ያሉትን አካል በስም ከመጥቀስ የተቆጠቡ ሲሆን በተደጋጋሚ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ የተገለጸለት መሆኑን ነገር ግን የአማራ ክልልን ለማመስ ካለው እቅድ የተነሳ በእኩይ ተግባሩ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በቅማንትና በአማራ ህዝብ መካከል የተጀመረው ግጭት ከሰሞኑ መበርታቱንና በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ገልጸዋል።
የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር ለመግለጽ የሚቻልበት ሁኔታ የለም ያሉት ሃላፊው አቶ አሰማህኝ በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውንና ንብረት መውደሙን ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ቀናት በሽንፋና ገንዳውሃ አካባቢዎች በሁለቱ ወገኖች መካከል የከረረ ግጭት እንደነበርም ሃላፊው ለኢሳት በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ አስታውቀዋል። ዛሬ አንጻራዊ የሆነ ሰላም መኖሩንም ጭምር።
የተከሰተውን ግጭት ለማብረድ የአማራ ክልል መንግስት የጸጥታ ሃይሉን በማሰማራት ሁኔታውን በመቆጣጠር ላይ መሆኑን አቶ አሳማሀኝ አስረስ ገልጸዋል።
የቅማንትና የአማራ ህዝቦች ያነሱትን መሳሪያ እንዲያስቀምጡ ጥሪ ያደረጉት አቶ አሰማህኝ የዘመናት አብሮነትን ለሌላ ቡድን መጠቀሚያ በማድረግ እንዳይሸረሽሩት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ወደ ገንዳውሃ ያመሩት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም በጉዳዩ ዙሪያ ከአካባቢው ህዝብ ጋር ተወያይተዋል ብለዋል።