በቄሌም ወለጋ ባንኮች ተዘረፉ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 6/2011)በቄሌም ወለጋ የኦነግ ታጣቂዎች ባንኮችን ዘረፉ።

የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ማቃጠላቸውም ተሰምቷል።

የቄሌም ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ ለኢሳት እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ቀናት በኦነግ ታጣቂዎች ስድስት ባንኮች ተዘርፈዋል። ሁለት የወረዳ የመንግስት መስሪያቤቶች ተቃጥለዋል።

በመንግስትና በግል ባንኮች ላይ በተፈጸመው ዝርፊያ ምን ያህል ገንዘብ መወሰዱን ማወቅ አልተቻለም።

ኦነግ በዞኑ ግድያን ጨምሮ የተለያዩ የሽብር ተግባራትን መፈጸሙን የሚያመለክቱ መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው።

በሌላ በኩል አየር ሃይል የኦነግን ካምፖች በአውሮፕላን መምታቱን በመግለጽ የወጡ ዘገባዎችን የኢሳት የአየር ሃይል ምንጮች የተሳሳተ ሲሉ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የቄሌም ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታመነ ሃይሉ ለኢሳት እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ቀናት በኦነግ ታጣቂዎች 3 የመንግስትና 3 የግል ባንኮች ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል።

ባንኮቹ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የህብረት ስራ ባንኮች ሲሆኑ በተለያዩ የቄሌም ወረዳ ቅርንጫፍ ከፍተው የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑ አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

የተዘረፈው የባንኮቹ ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ለጊዜው እንደማይታወቅ የገለጹት አቶ ታመነ በሂሳብ ሰራተኞች ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ጥቃት የደረሰባቸው ሌሎች ተቋማት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ናቸው።

በቄሌም ወለጋ ዞን የተለያዩ የወረዳ ጽሕፈት ቤቶችን ማቃጠል የኦነግ ስትራቴጂ መሆኑ እየተነገረ ነው።

የቄሌም ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታመነ ሃይሉ እንደገለጹት በሰሞኑ ጥቃት ሁለት የወረዳ የመንግስት ጽሕፈት ቤቶች በኦነግ ታጣቂዎች በተወሰደባቸው ርምጃ ተቃጥለዋል።

በአካባቢው የመንግስት ሃይል በሚደርስበት ጊዜ የኦነግ ታጣቂዎች በመሸሽ ሌላ አካባቢ እንደሚሄዱና ተመሳሳይ የዘረፋና የማውደም ርምጃ እንደሚወስዱ ነው አቶ ታመነ የሚገልጹት።

አፈናና ግድያ ለወራት በአካባቢያቸው እንደነገሰም አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

መንግስት ርምጃ መውሰድ በመጀመሩ በግድያና አፈና ላይ የኦነግ አቅም እንደቀድሞ አለመሆኑ ተመልክቷል።

አቶ ታመነ እንደሚሉት ቀሪ ባንኮችን ከዘረፋ ለማስጣል የመንግስት ተጨማሪ ሃይል ወደ አካባቢው በመግባት ጥበቃ እያደረገ ነው።

ህብረተሰቡን በማስተባበር የመከላከል ርምጃ በመወሰድ ላይ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በዚሁ ሰሞን የኦነግ ታጣቂዎች ከምዕራብ ወለጋ ዞን 11 ባንኮች ላይ ዘረፋ መፈጸማቸው መዘገቡ ይታወሳል።

በድምሩ ባለፉት አራት ቀናት በወለጋ ከ17 በላይ ባንኮች ላይ ዘረፋ የተፈጸመ ሲሆን የገንዘቡ መጠን እንደማይታወቅ ነው የተገለጸው።

ከሶስት ሳምንት በፊት በጉጂ ዞን ከሻኪሶ 6 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ጭኖ በሚሄድ የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ አጀብ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት የፈጸመው የኦነግ ቡድን ተሽከርካሪዎቹን የሚጠብቁ ሁለት የመንግስት ወታደሮች መግደሉ የሚታወስ ሲሆን ገንዘቡ በአንደኛው ተሽከርካሪ ሾፌር አማካኝነት ከዘረፋ መትረፉ ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ አየር ሃይል አውሮፕላኖች በወለጋ የኦነግ ወታደራዊ ካምፖችን መደበደባቸውን በተመለከተ የወጣውን ዘገባ የተሳሳተ ነው ሲሉ የኢሳት የአየር ሃይል ምንጮች ገልጸዋል።

የአየር ሃይል አዛዥ ዙሪያ ያሉ ምንጮች እንደገለጹት የተለመደ መደበኛ የቅኝት በረራ ከማድረግ ያለፈ በአውሮፕላን የተፈጸመ ጥቃት የለም።

ይህን የምንጮችን መረጃ ወታደራዊ ባለሙያዎችም ይደግፉታል።

የቀድሞ የአየር ሃይል አብራሪና የበረራ መመህር ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ ለኢሳት እንደገለጹት ዘገባው የተጋነነ፣ ከወታደራዊ ሳይንስና አሰራር ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ነው።

የኦነግን አቅም ለማግዘፍ የተደረገ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሊሆን ይችላል ተብሏል።