(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 26/2011) በኦሮሚያ ክልል በሌብነት ተጠርጥረው የታሰሩ ከንቲባዎች ቁጥር ሶስት ደረሰ።
በአጠቃላይ ከ70 በላይ የስራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ክልል የጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ሲሳይ ነጋሽ ትላንት ከሌሎች አራት ሰዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ቀደም ሲል የሻሸመኔና የገላን ከተማ ከንቲባዎች የነበሩ ሃላፊዎች መታሰራቸው ይታወሳል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ሲሳይ ነጋሽ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሃገር ሃብት አባክነዋል በሚል እንደሆነም የኦሮሚያ ክልል የጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል።
ከእነዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘም ከርሳቸው ጋር ሌሎች 4 ሰዎች መታሰራቸውም ተመልክቷል።
የኦሮሚያ ክልል የጸረ ሙስና ኮሚሽን በክልሉ ከተፈጸመ ዝርፊያ ጋር በተያያዘ የጀመረው ምርመራ በሳምንታት ውስጥ ከ75 በላይ የስራ ሃላፊዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ መሆኑ ታውቋል።
የታሰሩትም ሰዎች ከ86 ሚሊየን ብር በላይ የህዝብ ሃብት ዘርፈዋል በሚል እንደሆነም ተመልክቷል።
እስካሁን በሌብነት ተጠርጥረው ከታሰሩት የስራ ሃላፊዎች ውስጥ ከቀድሞው የአዳማ ከተማ ከንቲባ በተጨማሪ የሻሸመኔና የገላን ከተማ ከንቲቦችም ይገኙበታል።