ሜቴክ ከግማሽ በላይ ሰራተኞቹን ቀነሰ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 26/2011)የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን/ሜቴክ/ካሉት 19 ሺ 5 መቶ ሰራተኞች ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን መቀነሱ ተነገረ።

መንግስታዊውና ወታደራዊው ተቋም ሜቴክ ሰራተኞቹን ወደ ሌላ መስሪያቤት በማዛወርና በማባረር 8ሺ ብቻ እንዲቀሩት አድርጓል።

የሜቴክ የቀድሞ አመራሮች ከፍተኛ የሃገር ሃብት በማባከንና በሌብነት ተጠርጥረው ከተያዙ በኋላ ተቋሙን የማስተካከል ርምጃ ሲወሰድ ቆይቷል።

ሜቴክ ሰራተኞችን በማዛወርና በማባረር የቀነሰው አሁን ካለበት ውድቀት ራሱን ለማውጣት መሆኑን የተቋሙ አመራሮች ይናገራሉ።

በዚሁም መሰረት አምስት እቅዶችን በማዘጋጀት የሰራተኞችን ቁጥር ከ19ሺ 5 መቶ ወደ 8ሺ ዝቅ እንዲል መደረጉ ነው የተገለጸው።

ከሰራተኞቹ ብዙዎቹ ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ሲዛወሩ የተወሰኑት ደግሞ መንግስታዊ ወደ ሆኑ ሌሎች ተቋማት ተመድበዋል።

በኮንትራት የተቀጠሩ፣በፕሮጀክት ውስጥ የነበሩና አዲስ ራዕይ በተባለ ተቋም ስልጠና ላይ የነበሩ ሰራተኞች ግን ሙሉ በሙሉ ከስራ የተሰናበቱ መሆኑ ታውቋል።

ወደ መከላከያ ኢንደስትሪዎች  የተዛወሩት 5ሺ የሚጠጉ የሜቴክ ሰራተኞች ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ በመከላከያ ሚኒስቴር ስር በተዋቀሩት የጥይት ፋብሪካዎች የጥይት ፋብሪካዎች ተመድበዋል ተብሏል።

ሌሎች 2ሺ 5 መቶ የሚሆኑ የሜቴክ ሰራተኞች ግን ከስኳር ፕሮጀክቶችና ከሕዳሴው ግድብ ስራ ሙሉ በሙሉ የተሰናበቱ መሆናቸውን አዲስ ፎርቹን የተባለው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ዘግቧል።

2 ሺ 4 መቶ የሚሆኑት የሜቴክ ተቀጣሪ ሰራተኞች አዲሰ ራዕይ ከተባለ የስልጠና ተቋም ከተመረቁ በኋላ አታስፈልጉም ተብለው ከስራ ተሰናብተዋል።

ሜቴክ ያለበትን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍና ባቀዳቸው ስራዎች ላይ ለማተኮር 14 ቢሊየን ብር የሚያወጡ ንብረቶቹን በጨረታ ለመሸጥ አስቧል ተብሏል።

እነዚህ ንብረቶች በኦዲት ምርመራ ያለአገልግሎት የተገኙ ቁሶች ናቸው።

ሜቴክ በሁለት ተከፍሎ የሲቪልና ወታደራዊ ቁሶችን ለማምረት በአዲስ መልክ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ታውቋል።