(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 24/2011) የትግራይ ክልላዊ መንግስት የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ ተጠርጣሪዎችን ከለላ በመስጠት በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዳይውሉ እያደረገ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሐኑ ጸጋዬ አስታወቁ።
የቀድሞውን የደኅንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን ለመያዝ ስንጠይቅም የትግራይ ክልላዊ መንግስት ፈቃደኛ አይደለም ብለዋል።
እናም አቶ ጌታቸው አሰፋን ለመያዝ ስንል ጥይት ተታኩሰን የሌላ ሰው ሕይወት እንዲያልፍ አንፈልግም ብለዋል።
የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ በትግራይ ክልል ተሸሽገው እንደሚገኙ መንግሥት መረጃ እንዳለው ዋና አቃቤ ህግ ብርሃኑ ጸጋዬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸዋል።
ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የአምስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንዳሉት በዜጎች ላይ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም በማድረግ የተጠረጠሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋን በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል የክልሉ መንግሥት አሳልፎ እንዲሰጥ ጥያቄ ቀርቦለታል።
ይሁንና ክልሉ ትብብር ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለም ነው ያሉት።
ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ውጪም የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ ተጠርጣሪዎችን የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከለላ እንደሰጠና በሕግ ቁጥጥር ሥር ማዋል አለመቻሉን ገልጸዋል።
እነዚህ ከለላ የተሰጣቸው ከክልሉ ወጪ ተወላጂ የተባሉ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
‹‹ተጠርጣሪውን ለመያዝ ጥይት በመታኮስ የሌላ ሰው ሕይወት እንዲያልፍ አንፈልግም፤›› በማለት የኃይል ርምጃ ያልተወሰደበትን ምክንያት ጠቁመዋል።
እናም ፓርላማው በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም ይዞ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ማብራራያ አልተደሰቱም።
መንግሥትም ሆነ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በዚህ ጉዳይ ላይ ፈራ ተባ ሊሉ እንደማይገባ አንድ የምክር ቤት አባል አሳስበዋል።
በደል የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን መንግሥት በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ሳይችል ስለሕግ የበላይነት ማውራት እንደማይችልም ነው የገለጹት።
ለሌሎች ተጠርጣሪዎችም የሚሰጠው ትርጉም ወንጀል ፈጽሞ ብሔር ውስጥ መሸሸግ የሚቻል መሆኑን ነው በማለት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑን ማብራሪያ ተችተዋል።
ተጠርጣሪውን ለመያዝ ያስቸገረው ምንድን እንደሆነ፣ ምናልባትም ግለሰቡ ያለመከሰስ መብት ይኖራቸው እንደሆነም የምክር ቤቱ አባል ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ በሰጡት ምላሽ፣ ተጠርጣሪው አቶ ጌታቸው የክልልም ሆነ የፌዴራል ምክር ቤት አባል እንዳልሆኑና ያለመከሰስ መብት እንደሌላቸው አስታውቀዋል።