በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 24/2011) በቡራዩ ከተማ ከተከሰተው ግጭትና ግድያ ጋር በተያያዘ በ109 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለጸ።

በሃዋሳ ከተማ ከተነሳው ግጭት ጋር በተያያዘም በወቅቱ የሃዋሳ ከተማ ከንቲባና የፖሊስ አባላትም ተሳታፊ እንደነበሩም ከጠቅላይ አቃቤ ህግ መግለጫ መረዳት ተችሏል።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ የስራ ሃላፊዎች ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በቡራዩ ከተማ ከተነሳው ግጭት ጋር በተያያዘ 649 ሰዎች ተይዘው እንደነበር አስታውሰዋል።

በመስከረም ወር 2011 በአዲስ አበባ አቅራቢያ ቡራዩ ከተማ ከተፈጸመው ግጭትና ግድያ ጋር በተያያዘ በተደረገው ማጣራት በቀጥታ በግድያና በማነሳሳት ተሳታፊ በሆኑት ላይ ክስ መመስረቱን ገልጸዋል።

በመጨረሻም በተደረገው ማጣራት 113 ሰዎች የተለዩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 13ቱ በፍርድ ቤት በዋስትና መለቀቃቸውን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በቀጥታ በግድያው በመሳተፍና በማነሳሳት በተጠረጠሩ 109 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን የአቃቤ ህግ ሃላፊዎች ገልጸዋል።

ከነዚህ ውስጥ 81 በእስር ላይ ሲሆኑ 28ቱ በሌሉበት ክስ እንደተመሰረተባቸውም ገልጸዋል።

እነዚህ 28 ሰዎች የፍርድ ቤት ማዘዣ መጥቶባቸው እየታደኑ መሆኑንም ገልጿል።

ግጭቱና ግድያው ብሔርን መሰረት ያደረገ ማነሳሳት የነበረበትና ለውጡንም ጭምር ለማደናቀፍ ያለሙ ወገኖች የተሳተፉበት እንደሆነም ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል።

የቡራዩን ግድያና ግጭት ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የጸጥታ ችግር በፈጠሩ ግለሰቦች ላይም ክስ መመስረቱን የአቃቤ ህግ ሃላፊዎች ጨምረው ገልጸዋል።

በሃዋሳ ከተማ በወላይታ ተወላጆች ላይ ከደረሰው ጥቃት ጋር በተያያዘ የሃዋሳ ከተማ ከንቲባና የፖሊስ አባላት ተሳታፊ ነበሩ ያለው አቃቤ ህግ በነዚህም ላይ ክስ መመስረቱን አመልክቷል።

በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ የጸጥታ ችግሮችም በተደራጀ ሁኔታ የሚካሄድ መሆኑን አስረድቷል።