በተለያዩ አካባቢዎች የዜጎች ግድያና መፈናቀል ቀጥሏል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 24/2011) በደቡብ ኢትዮጵያ በካፋ ዞን ብሔርን መነሻ ባደረገ ግጭት ከ10 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ፍንጭ ውሃ ከተማ ላይ ተመሳሳይ ብሄር ተኮር ጥቃት ተሰንዝሮ 15 ሰዎች መገደላቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ፋይል

በሌላ በኩል ከሁለት ዓመት በላይ ሰላም በማጣት ቆይተናል የሚሉት የአማሮ ኬሌ ወረዳ ነዋሪዎች በኦነግ ታጣቂዎች የሚደርስባቸው ጥቃት በመቀጠሉ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ዞኖች ተከስቶ የነበረውን ግጭትና መፈናቀል ሙሉ በሙሉ መቆሙን በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስታውቋል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ድርቅ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች ለም ወደ ሆኑ የክልሉ ወረዳዎች የሰፈራ ፕሮግራም የተካሄደው ከ15 ዓመታት በፊት ነበር።

ከከምባታ ጠምባሮ፣ ከሲዳማና ከወላይታ አካባቢዎች በሰፈራ ፕሮግራም ታቅፈው በካፋ ዞን ለም ወረዳዎች ኑሯቸውን የጀመሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ላለፉት 15 ዓመታት ቤተሰብ መስርተው ኑሯቸውን ቀጥለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ማንነትን መነሻ ባደረገ ጥቃት ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በካፋ ዞን ደቻ ወረዳ ሻሎ ቀበሌ ነዋሪ በሆኑ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በተመለከተ ኢሳት ያነጋገራቸው ሰዎች እንደሚሉት በይዞታነት ከሚገለገሉባቸው ቦታዎች እንዲለቁ በቀበሌ አመራሮች የተላለፈውን ውሳኔ ባለመቀበላቸው ጥቃቱ እየደረሰባቸው ነው።

አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ በሚል እየተፈጸመ ባለው ጥቃት ከ10 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

ህጻናትና በእድሜ የገፉ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ለቀናት የዘለቀው ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ዳግም ግጭት አገርሽቶ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ በተፈጸመ ጥቃት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በዞኑ ማንነትን መሰረት ባደረገው ጥቃት እስካሁንም ከ15 ያላነሱ ሰዎች በጥቃቱ መገደላቸው ታውቋል።

ከጉጂ ዞን በምትዋሰነውና በደቡብ ክልል ስር በምትገኘው የአማሮ ልዩ ወረዳም ሰላም ማጣቷ ቀጥሎ ሰሞኑን በኦነግ ታጣቂዎች በሚፈጸመው ጥቃት 4 ሰዎች መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የኦነግ ታጣቂዎች በአማሮ ኬሌና በዙሪያዋ በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት የሚያስቆመው አካል አልተገኘም በሚል ነዋሪው ምሬቱን በመግለጽ ላይ ነው።

የኦነግ ታጣቂዎች የእርሻ ማሳ ማቃጠል፣ ከብቶችን መዝረፍና ግድያ በመፈጸም አካባቢውን ሰላም አሳጥተውታል ሲሉ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

ባለፈው ቅዳሜ የኦነግ ታጣቂዎች የምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ሶስት አመራሮችን አፍነው መውሰዳቸው መዘገቡ ይታወሳል። አመራሮቹ እስካሁን የት እንደተወሰዱ የተገለጸ ነገር የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ዞኖች ተከስቶ የነበረውን ግጭትና መፈናቀል ሙሉ በሙሉ መቆሙን በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስታውቋል።

ለውጡን በማይደግፉ ሃይሎች በኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ እና በምስራቅ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋ፣ በሆሮ ጉዱሩ፣ በኢሉ አባቦራ እና ቡኖ በደሌ ዞኖች ሰላማዊ እንቅስቃሴን በመገደብ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱን ሲያፍኑ ነበር ያለው ኮማንድ ፖስቱ በተወሰደው ርምጃ አሁን ሁሉ ነገር ቆሟል ብሏል።

በቤንሻንጉል ጉምዝም ካማሽ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች እና በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ ማንነታቸው ያልታወቁ የታጠቁ ህገ ወጥ ቡድኖች ተመሳሳይ ችግር ሲፈጥሩ ቢቆዩም በተወሰደው ርምጃ ሰላም መገኘቱን ነው ኮማንድ ፖስቱ ያስታወቀው።

የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሆነም ተገልጿል።