(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 23/2011) በምዕራባውያኑ 2018 ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሞከሩ 1300 ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የ2018 መጨረሻን ምክንያት በማድረግ ባወጣው ሪፖርት ወደ ጣሊያንና ማልታ ለመሻገር የሞከሩ 1ሺህ 300 ስደተኞች ህይወታቸው አልፏል።
አለም አቀፉን የስደተኞች ድርጅት IOMን በመጥቀስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳስታወቀው ብዙዎቹ ሟቾች የቱኒዚያ፣ ኤርትራ፣ ኢራቅ፣ ሱዳን፣ ፓኪስታን እና የናይጄሪያ ዜጎች ናቸው።
የጣሊያን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው በተጠናቀቀው የምዕራባውያኑ 2018 ወደ ጣሊያን የተሻገሩ ስደተኞች ቁጥር በ80 በመቶ ቀንሷል።
በ2017 ጣሊያን የደረሱ ስደተኞች ቁጥር 23ሺህ 370 እንደነበርም ከጣሊያን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት መረዳት ተችሏል።
በሊቢያ አድርገው ወደ አውሮፓ የሚሻገሩት ስደተኞች ቁጥር የቀነሰው በጣሊያንና በሊቢያ መንግስታት መካከል በተደረገ ስምምነት እንደሆነም ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በዚሁ የምዕራባውያኑ 2018 ማብቂያ በመጥፎ የአየር ጸባይ ሳቢያ በባህር ላይ ለአደጋ የተጋለጡ 180 ስደተኞችን የማልታ መንግስት ከአደጋ ታድጓል።
በሜዲትራንያን ባህር ላይ ለአደጋ ተጋልጠው የነበሩት 180 ሰዎች ቢተርፉም ሌሎች 49 ሰዎች በሌላ መርከብ ላይ ለአደጋ መጋለጣቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጀልባው በአውሮፓ ማረፊያ እንዲያገኝ ጥሪ አቅርቧል።