(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 22/2011) በኦሮሚያ ክልል ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የተፈናቀሉ የአማራ ተማሪዎች ሁኔታዎች ሲመቻቹ ወደ ትምህርታቸው እንደሚመለሱ የአማራ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ፡፡
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ጥር 1 እና 2 ተማሪዎችን ለመመለስ እቅድ መያዙም ታውቋል
በቡሌ ሆራ እና አካባቢው ተከስቶ በነበረው ግጭት ዩኒቨርሲቲው በሴኔቱ ስምምነት ለጥቂት ቀናት እንዲዘጋ ተወስኗል ፡፡
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአካባቢው በተፈጠረ የሰላም እጦት ምክንያት ወደ የመጡበት አካባቢ ተመልሰዋል፡፡
በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታታሉ የነበሩ የአማራ ክልል ተማሪዎችም ዩኒቨርሲቲው ትምህርት በማቋረጡ ምክንያት ባህር ዳር ገብተዋል፡፡
ተማሪዎቹ ለውጡን በማይፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች ችግሩ ሌላ መልክ ይዞ ከትምህርታችን ተስተጓጉለናል ብለዋል፡፡
ለመማር ማስተማሩ መቋረጥ ምክንያት በሆኑ ግለሰቦች ላይ ዩኒቨርስቲው ህጋዊ ርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ ሌላ መልክ እንዲይዝ ሆኗል ነው ያሉት ተማሪዎቹ፡፡
እናም የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስት ችግሩን በአፍጣኝ ፈትቶ ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሡ ጠይቀዋል ፡፡
ተማሪዎቹ ችግሩ የጥቂት ግለሰቦች ሴራ ነው፤ ማንንም አይወክሉም ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት በበኩሉ ችግሩ ከተፈጠረበት ቀን ጀምሮ ከጎናቸው ሆኖ እየሰራ እንደሆነ እና ወደፊትም ችግሩ በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ እሰራለሁ ብሏል፡፡
የአማራ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ መንግስታቸው ችግር የመስማት ብቻ ሳይሆን መፍትሔ ማምጣት አለበት ብለዋል፡፡
ችግሩም ከፌዴራል መንግስት እና ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር በመተባበር ይፈታል ነው ያሉት፡፡
እናም በዩኒቨርስቲው እና በአካባቢው የተፈጠረው ግጭት ሲረጋጋ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲው ይመለሳሉ ብለዋል፡፡
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲም ጥር 1 እና 2 ተማሪዎችን ለመመለስ ማቀዱን አስታውቋል፡፡
ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ የተፈናቀሉ የአማራ ተማሪዎች ቋሚ መፍትሄ እስኪመቻች ድረስ በባህር ዳር አለም አቀፍ ስታዲየም ግቢ ባሉ ክፍሎች መኝታ ተዘጋጅቶላቸው እንዲያርፉ ተደርጓል።