በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ውስጥ አደገኛ መርዝ አለ ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 22/2011)በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ውስጥ አደገኛ መርዝ መኖሩን የተቋሙ ሰራተኞች የነበሩ እስረኞች ገለጹ።

ይህንኑ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ያሳወቀ ሲሆን የመርዙ አይነትና አደገኝነት በባለሙያ እየተመረመረ መሆኑም ተመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኦነግና የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትን ማሰርና ማሰቃየት  ህጋዊ አሰራር ስለነበር ልንጠይቅ አይገባም ሲሉ ታሳሪ የደህንነት አባላት መናገራቸውን ሪፖርተር በዘገባው አስፍራሯል።

በሌላም በኩል የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤትም በህግ ሊጠየቅ ይገባል ሲሉ ተከሳሾቹ መናገራቸውም ታውቋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ባልደረባ በነበሩት በአቶ ጎሃ አጽብሃ የምርመራ መዝገብ በምርመራ ላይ የሚገኙት ተከሳሾች አደገኛ መርዝ በተቋማቸው ውስጥ መኖሩን ለፖሊስ መግለጻቸውን አመልክተዋል።

እነርሱም ራሳቸው በሰጡት መረጃ መሰረት አደገኛ መርዝ መኖሩን ያወቀው ፖሊስ በምርመራ የደረሰበት በማስመሰል ለፍርድ ቤት ማቅረቡን ተቃውመዋል።

ፖሊስም መረጃውን ተከሳሾቹ እንደሰጡት አረጋግጧል። ሆኖም የመርዙ አይነትና የጉዳት መጠን በባለሙያዎች እየተመረመረ መሆኑን ነው የተገለጸው።

እነዚሁ ተከሳሾች ይሰሩበት የነበረው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤትም በተቋም ደረጃ አብሮ ሊከሰስ ይገባል ሲሉ መጠየቃቸውን ከሪፖርተር ዘገባ መረዳት ተችሏል።

በተመሳሳይ የማሰቃየት ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት አቶ መአሾ ኪዳኔና በግብረአበርነት የተከሰሱት የተቋሙ ሰራተኞች ኦነግና አርበኞች ግንቦት 7 በፓርላማ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ በመሆናቸው የነርሱን አባላት ማሰርና ማሰቃየት ሊያስጠይቀን አይገባም ሲሉ መከራከራቸውንም ከዘገባው መረዳት ተችሏል።