(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 18/2011) ለኢትዮጵያ ግዙፍ መንግስታዊ የፋይናንስ ተቋማት ሁለት ታዋቂ ኢኮኖሚስቶች በቦርድ ሊቀመንበርነት ተሰየሙ።
ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተባበሩት መንግስታት የሚሰሩት ዶክተር ኢዮብ ተስፋዬ በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመረጡ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ልማት ፕሮግራም ሪጅናል ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር ተገኘወርቅ ጌጡ መመረጣቸው ታውቋል።
የመንግስት የገንዘብ ተቋማት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዳይሬክተር እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ በማክሮ ኢኮኖሚስትነት ሲያገለግሉ ቆይተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የተቀላቀሉት ዶክተር ኢዮብ ተስፋዬ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር እንዲሆኑ መመረጣቸውን የዘገበው አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ነው።
ለኢሳት በደረሰው መረጃ የኢትዮጵያ ግዙፍ የገንዘብ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዶክተር ኢዮብ ተስፋዬ በተጨማሪ አዳዲስ የቦርድ አባላት መምረጡ ታውቋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ማሞ ምህረቱ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ በየነ ገብረ መስቀል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን ስራ አስፈጻሚ ፣ዶክተር አብርሃም በላይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ኦዲተር ዳይሬክተር፣ አቶ ገመቹ ዲቢሞ ከተመረጡት የቦርድ አባላት ውስጥ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በመስጠት የባንኩን ጤናማነት ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባ በባለሙያዎች ሲገለጽ ቆይቷል።
በቢሊየን ብር የሚቆጠሩ ብድሮች የተበላሸ እየተባሉ በትዕዛዝ ሲሰረዙ መቆየታቸውም በስፋት ተዘግቧል።
አቶ አባይ ጸሃዬና አቶ በረከት ስምኦን የቦርድ ሊቀመንበርነቱን ስፍራ በያዙበት ወቅት በተለይም በአቶ አባይ ጸሃዬ ትዕዛዝ ባንኩ ሲመዘበር መቆየቱን የባንኩ ምንጮች ይገልጻሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተነስተው ከመስኩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ዶክተር ተገኝወርቅ ጌጡ የተሾሙት ማክሰኞ ታህሳስ 16/2011 መሆኑም ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የክፍለ ሃጉር ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር ተገኝወርቅ ጌጡ ጋር አዳዲስ የቦርድ አባላት መሾማቸውንም ከአዲስ ፎርቹን ዘገባ መረዳት ተችሏል።
የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ዶክተር ዩሃንስ አያሌው፣ የቀድሞ የግብርና ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው እንዲሁም የአሁኑ የግብርና ሚኒስትር ኡመር ሃሲንና የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ መስፍን አማረ የልማት ባንክ ቦርድ አባላት ሆነው መመረጣቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሆነ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተመረጡት የቦርድ ሊቀመንበሮች የመስኩ ባለሙያዎች ከመሆናቸው ባሻገር የፓርቲ አባል ያልሆነ ሰው ሲሾምም የመጀመሪያው መሆኑም ታውቋል።