በኢሳና አፋር ብሄረሰቦች ግጭት 8 ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 18/2011) በኢሳና አፋር ብሄረሰቦች መካከል የተከሰተው ግጭት ቀጥሎ በዛሬው ዕለት 8 ሰዎች መገደላቸው ታወቀ።

ከአዲስ አበባ እስከጅቡቲ በተዘረጋው መንገድ ላይ በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች የሁለቱ ወገኖች ግጭት ሲካሄድባቸው እንደዋለ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ፋይል

ዛሬ ገዳማይቱ ላይ በተካሄደ ግጭት ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ከሮማ በተሰኘች መንደር የአንድ ሰው ህይወት አልፏል።

ከሰኞ ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የአፋርና የኢሳዎች ግጭት ወደ ሰላሳ የሚጠጋ ሰው መገደሉን ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።

መከላከያ ሰራዊት የበላይ ትዕዛዝ አልደረሰኝም በማለት ግጭቱን ማስቆም እንዳለቻለም ተገልጿል።

ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የተዘረጋው መንገድ ላይ አለፍ አለፍ ብለው የከተሙ መንደሮች ካለፈው ሰኞ ወዲህ ጥሩ ነገር አይታይባቸውም።

ብረት ባነሱ ሁለት ወገኖች ግጭት ሰላም ርቋቸው ነው የከረሙት።

ለመጪውም በዚሁ መዝለቃቸው እንጂ የራቃቸውን ሰላም ማግኘታቸውን የሚያመለክት ፍንጭ የለም።

በዛሬው ዕለት ብቻ ስምንት ሰዎች የተገደሉበት ግጭት ከዚያው አካባቢ መከሰቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በኢሳና አፋር ማህበረሰቦች መካከል ለዘመናት ያዝ ለቀቅ እያደረገው የዘለቀው ግጭት ሰሞኑን ከረር ጠንከር ብሎ እየተካሄደ መሆኑን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

ከሰኞ ጀምሮ በተካሄደው ግጭት ከሁለቱም ወገኖች ሰላሳ ሰዎች ተገድለዋል።

የዛሬ ግጭት የተከሰተው ገዳማይቱ በተሰኘች ከተማ ነው።

በአፋር ክልል ስር በምትገኘው ገዳማይቱ ላይ የኢሳ ታጣቂዎች ሰነዘሩ የተባለውን ጥቃት ለመመከት የአፋር ልዩ ሃይል በወሰደው ርምጃ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ አምስት መቁሰላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከሮማ በተሰኘች መንደርም በተመሳሳይ ግጭት እንደነበረና የአንድ ሰው ህይወት መጥፋቱ ታውቋል።

የአፋር ልዩ ሃይልና የኢሳ ታጣቂዎች እያካሄዱት ያለው ግጭት በተለይም በአዋሽ አርባ፣ ገለአሉና ገዳማይቱ በተባሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ እየተካሄደ እንዳለ ይነገራል።

መከላከያ ሰራዊት በሚፈለገው መጠን ግጭቱን ለማስወገድ እየወሰደ ያለው ርምጃ በቂ አይደለም በሚል ይተቻል።

በአንዳንድ መከላከያ በደረሰባቸው አካባቢዎች ግጭቱ መብረድ የቻለ ሲሆን በተወሰኑ ግጭቱ በበረታባቸው አካባቢዎች ግን የመከላከያ ዝምታ አደጋውን እንዲጨምር አድርጎታል እየተባለ ነው።

የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ገአአስ አህመድ ለኢሳት እንደገለጹት የህወሃት እጅ በሰፊው የገባበት የሰሞኑ ግጭት በማህበራዊ ሚዲያዎች ቀደም ብሎ የታወጀ ነው።

የህወሃት የፌስ ቡክና ቲውተር ሰራዊት በኢሳዎችና በአፋሮች መካከል በቅርቡ ግጭት ይኖራል ብለው መረጃ ሲያሰራጩ እንደነበረ የሚገልጹት አቶ ገአስ የሰሞኑ ግጭት በእቅድ የተነደፈ መሆኑን ከበቂ በላይ ማስረጃ አለን ይላሉ።

የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር አርዱፍ ወይም በአፋርኛ ኡጉጉሙ በመባል የሚታወቀው ታጣቂ ድርጅት የሰሞኑን ጥቃት በማቀነባበርና በመሳሪያ በመደገፍ ህወሃትንና የጅቡቲን መንግስት ይከሳል።

በጉዳዩ ላይ የጅቡቲ መንግስት እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።

በተያያዘ ዜና የአፋር ወጣቶች ከጅቡቲ አዲስ አበባ በተዘረጋው መንገድ ላይ ህገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድና የጦር መሳሪያ ዝውውር እየተካሄደ ነው በሚል ለተወሰኑ ሰዓታት መንገዱን ዘግተው እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።

ወጣቶቹ በህወሃት አጋዥነት ኢሳዎች መሳሪያ ከአንድ ቦታ ወደሌላ በማዘዋወር ላይ ናቸው በሚል ርምጃውን መውሰዳቸውን ገልጸዋል።