ድንበር ተሻግረው የገቡ ሃይሎች 22 ኢትዮጵያውያንን ገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 18/2011)በኢትዮጵያና ሶማሊያ ድንበር የተሻገረ የታጠቀ የውጭ ሃይል ጥቃት ከፍቶ 22 ኢትዮጵያውያንን ገደለ።

የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በኢትዮጵያ የድንበር ከተማ ገሃንዳሌ ላይ በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት 50 ሰዎች ቆስለዋል።

ትላንት ጠዋት ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ ወረራ በፈጸመው የውጭ ሃይል ከተገደሉትና ከቆሰሉት በተጨማሪ የገሃንዳሌ ነዋሪዎች አካባቢውን ጥለው መሰደዳቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአቅራቢያው ቢኖርም ዜጎችን ከጥቃት መከላከል እንዳልቻለ ግን ተገልጿል።

እንደወትሮው የጎሳ ግጭት አይደለም። በኢትዮጵያውያን መካከል የተደረገም አይደለም።

ድንበር በተሻገረ በዘመናዊ መሳሪያና ተሽከርካሪዎች በታጀበ ሃይል የተፈጸመ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንጂ።

በኢትዮጵያና በሶማሊያ የድንበር አካባቢ ወሰን ተሻጋሪ ግጭቶች እምባዛም ተከስተው እንደማያውቁ የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች ከአንድ ሳምንት ወዲህ ግን የኢትዮያን ድንበር ተሻግረው ጥቃት ለመፈጸም የተዘጋጁ ሃይሎች መኖራቸው መረጃው ነበር።

ርምጃ ባለመወሰዱ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን ድንበር በተሻገሩ የተደራጁ ታጣቂዎች ኢትዮጵያውያ ላይ ጥቃት ተሰነዘረ። –በርካቶች ተገደሉ። በርካቶች ቆሰሉ።

ኢትዮጵያን ከሶማሊያ በሚያዋስነው ቀንድ በሚመስለው ክፍል ባለው የዋርዴር ዞን ገላዲ ወረዳ ገሃንዳሌ መንደር ጥቃቱ የተፈጸመው ትላንት ነው።

ከሶማሊያ ተነስተው የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የገቡት ታጣቂዎች ከባድ መሳሪያ የታጠቁ መሆናቸውን የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ።

በቀላል መሳሪያ አማካኝነት የሚደረግ የጎሳዎች መለስተኛ ግጭት በአካባቢው የተለመደ ቢሆንም የዚህ ሰሞን የሆነው ግን የተለየና ጉዳቱ ከባድ ነበርም ይላሉ።

በበርካታ ተሸከርካሪዎች የተጫኑ በመቶዎች የሚቆጠሩት ታጣቂዎች የገሃንዳሌን መንደር በመውረር ለዘጠኝ ሰዓታት የዘለቀ ጥቃት ሰንዝረዋል።

22 ኢትዮጵያውያንን በመግደልና 50ዎቹን በማቁሰል ምሽት ከመምጣቱ በፊት አካባቢውን ለቀው ተመልሰው ወደ ሶማሊያ መግባታቸውን ነው ለማወቅ የተቻለው።

የውጭ ሃይል ድንበር አቋርጦ ጥቃት ፈጽሞ ኢትዮጵያውያንን ገድሎና አቁስሎ ሲወጣ የሚከላከል ሃይል አልነበረም።

የመከላከያ ሰራዊት በዋርዴር ዞን የሰፈረ ቢሆንም ርምጃ መውሰድ አለመቻሉን የገለጹት የኢሳት ምንጮች ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም የተሰወነ ሃይል በገላዲ ወረዳ ገሃንዳሌ መንደር አቅራቢያ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

መከላከያ ሰራዊት የውጭ ሃይል ድንበር ተሻግሮ ጥቃት ሲፈጽም መከላከል ያልቻለበት ምክንያትን ለማወቅ ምንጮች ያደረጉት ጥረት አልተሳካም።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ በተደጋጋሚ በገሃንዳሌ አካባቢ ያሉ ቦታዎች ይገባኛል የሚል ጥያቄ ያነሱ እንደነበር ታውቋል።

የመሬት መገፋፋት ለዘመናት የነበረ መሆኑን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች በዚህ መልኩ ጥቃት ተፈጽሞ እንደማያውቅም ይገልጻሉ።

ለአንድ ሳምንት ያህል ዝግጅት ሲደረግ መረጃው በክልሉ መንግስት እንደነበርም ታውቋል።

የተደራጁት የውጭ ሃይሎች ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸው እየታወቀ አስቀድሞ የመከላከል ርምጃ ያልተወሰደበት ምክንያንት ግራ የሚያጋባ ሆኗል።

የሶማሌ ክልል መንግስት ጉዳዩን በመመርመር ላይ እንዳለ የተገለጸ ሲሆን ከሰሞኑ መግለጫ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በጥቃቱ የቆሰሉት 50 ዜጎች በዋርዴርና በጂጂጋ ህክምና ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።

ለጊዜው ወደ መነሻ ቦታቸው የተመለሱት የውጭ ሃይሎች ዳግም ይመጣሉ በሚል ስጋት የገሃንዳሌ ነዋሪዎች አካባቢውን በመልቀቅ በአቅራቢያ ወዳሉ ወረዳዎች መፈናቀላቸውንም ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።