የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በመንግስት ላይ ድል ተቀዳጀሁ አለ

ታህሳስ 25 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-የዘመቻ ደምመላሽ ሰራዊት በሰሜን ጎንደር ላይ አርማጭሆ ዶጋው ልዩ ስሙ ጉርማጭት በተባለ አካባቢ ላይ በታህሳስ 21- 2004 ዓ.ም በመቶ አለቃ ገበየሁ ከሚመራው ልዩ ሃይል ጋር በተካሄደ ውጊያ 9 የመንግስት ልዩ ሃይል ታጣቂዎች መግደሉን፣  16ት ወታደሮችን ደግሞ ማቁሰሉን ገልጧል።

ከባድና ቀላል መሳሪያዎችን ከነ መሰል ጥይቶቻቸው ጋር መማረኩን ያስታወቀው  የኢሕአግ ወታደራዊ መምሪያ ፣

የዘመቻ ደምመላሽ ሰራዊት በተከታታይ እያካሄደ የሚገኘው ድንገተኛ ወታደራዊ ማጥቃት እርምጃ በመንግስት የመከላከያ ፤ የሚሊሻና የልዩ ሃይል ላይ ጫና እያሳደረ ነው ብሎአል።

ግንባሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተመሳሳይ ጥቃቶችን መሰንዘሩን እና ለአካባቢው ህዝብም የቅስቀሳ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን መንግስት ጋር በመተባበር በድንበር አካባቢ ያለውን የአማጽያን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

አርበኞች ግንባር ከእርሱ ወገን የሞቱበትን ወታደሮች ቁጥር አላስታወቀም። የኢትዮጵያ መንግስትም በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት አልሰጠም።