(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 10/2011) ከቅማንት የመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጥባቸው የቆዩ ሶስት ቀበሌዎችን በቁጥጥሩ ስር ማዋሉንየአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
ላለፉት ሶስት ዓመታት ከክልሉ መንግስት ቁጥጥር ውጪ ሆነው በቆዩት ጉባይ ጀጀቢት፣ሌንጫና መቃ በተሰኙ ቀበሌዎች የቅማንትን ጥያቄ በጉልበት ለመፍታት በሚፈልግ ሃይል አማካኘነት የተደራጀ ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጥባቸው መቆየቱን የኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ እነዚህ ቀበሌዎች ከክልሉ መንግስት ቁጥጥር ውጪ ሆነው ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጥባቸው እንደነበረ ለኢሳት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ሰሞኑን በአይከል ከተማ በተደረገ የሰላም ኮንፍረንስ ላይ እንደተገለጸው የአማራ ክልል መንግስት ሶስቱን ቀበሌዎች ያለአንዳች የተኩስ ልውውጥ በቁጥጥሩ ስር አድርጓል።
የኮሚኒኬሽን ቢሮው እንዳስታወቀው ከህዝቡ እና ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰሞኑን በተወሰደ ርምጃ ነው ቀበሌዎቹ ወደቀድሞ አስተዳደራቸው እንዲመለሱ የተደረጉት።
በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው የተመራ የአመራር ቡድንም በሦስቱም ቀበሌዎች በመግባት ከህዝቡ ጋር የተሳካ ውይይት ማድረጉም ተገልጿል።
ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ የክልሉን ደህንነት በአዲስ መልክ በማዋቀር ላይ ያተኮረ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሶስቱን ቀበሌዎች ከክልሉ መንግስት ቁጥጥር ውጪ አድርጎ ስልጠና በመስጠት ክልሉን ሲያተራምስ የነበረው ሃይል አሁን ከስልጣን የተወገደው የህወሃት ቡድን መሆኑን ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ለኢሳት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።