የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰጠው ብድር ከ550 ቢሊዮን ብር በለጠ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 10/2011)የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመንግስትና ለግል ኩባንያዎች ያበደረው ብድር ከ550 ቢሊዮን ብር መብለጡ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምንጮችለኢሳት እንደገለጹት ትልቁን ብድር የወሰደው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ሲሆን የስኳር ኮርፖሬሽንና የባቡር ኮርፖሬሽንበተከታይነት ከፍተኛ ብድር መውሰዳቸው ተመልክቷል።

ከ550 ቢሊዮን ብር ውስጥ 74 በመቶውን 6 የመንግስት ድርጅቶች የወሰዱ ሲሆን የዚህም ጠቅላላ ድምር 413 ቢሊዮን ብር ያህል እንደሆነም ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የብድሩ መጠን እየጨመረ መገኘት አሳሳቢ እንደሆነ የሚገልጹት ምንጮች ብድሩ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ መመለሱም አጠራጣሪ ነው ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተገኘው መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር ከሰጠው ከ550 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከፍተኛውን ብድር ማለትም 240 ቢሊዮን ብር የወሰደው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ሲሆን የስኳር ኮርፖሬሽን ብድር ደግሞ 88 ቢሊዮን ብር መድረሱም ታውቋል።

የባቡር ኮርፖሬሽን የወሰደው 30 ቢሊየን ብር የአዲስ አበባ ቤቶች 40/60 ፕሮጀክት 28 ቢሊየን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር የወሰደ ሲሆን ሜቴክ 16 ቢሊየን ብር ኬሚካል ኮርፖሬሽን ደግሞ 12 ቢሊየን ብር መውሰዳቸውን የባንኩ ምንጮች ገልጸዋል።

እነዚህ 6 የመንግስት ግዙፍ ተቋማት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱት ረዥም ግዜ ብድር በድምሩ 414 ቢሊየን ብር ሲሆን ከጠቅላላው ብድር ከ75% በላይ እንደሆነም ታውቋል።

ለመንግስት ተቋማት በየግዜው ሲሰጥ የቆየው  ብድር በባንኩ ላይ ጫና ማሳደሩ የተገለጹ ሲሆን በተቀመጠው የግዜ ገደብ ብድሩ መመለሱ አጠራጣሪ እንደሆነም ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ለህዳሴው ግድብ እና ለኪንዶ ካይሹ ግድብ ለኤሌክትሪክ ሃይል ትራንስሚሽንና ሌሎች ተጨማሪ ብድር ያስፈልገዋል የሚሉት ባለሙያዎች በዚህም የተነሳ በተቀመጠው ግዜ ገደብ ብድሩን ከፍሎ እንደማይጨርስ ገልጸዋል።

የ16 ቢሊየን ብር ዕዳ ያለበት ሜቴክ ከሌብነት ጋር በተያያዘ በርካታ ፕሮጀክቶቹን በመነጠቁ ዕዳውን መክፈሉ አጠራጣሪ እንደሆነም እነዚሁ ባለሙያዎች ያክላሉ።

ይህ ከፍተኛ ብድር ለተቋማቱ የተሰጠው አዋጪነት ጥናት ማይካሄድበት በሚል አቶ አባይ ጸሃዬ የቦርድ ሊቀመንበር በነበሩበት ወቅት እንደሆነም ተመልክቷል።

በሌላም በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር መጠኑ ከ100 ሚሊየን እስከ 4 ቢሊየን ብር የሆነ በድምሩ 16 ቢሊየን ብር ለ13 የግል ተበዳሪዎች መስጠቱንም የባንኩ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

ለ13ቱ ነጋዴዎች በድምሩ የ16 ቢሊየን ብር ብድር የተሰጠው አቶ አባይ ጸሃዬና አቶ በረከት ስምኦን የቦርዱ ሊቀመንበር በነበሩበት ጊዜ ሲሆን የባንኩ ፕሬዝዳንት የነበሩትም አቶ በቃሉ ዘለቀ መሆናቸው ተመልክቷል።

ከ13ቱ ነጋዴዎች ውስጥ ከፍተኛውን ብድር የወሰዱት የተክለብርሃን አምባዬ የኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤት አቶ ተክለብርሃን አምባዬ መሆናቸው ተገልጿል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱት 4 ቢሊየን ብር መሆኑም ታውቋል።

 በቀጣይነት ከፍተኛውን ብድር የወሰዱት የሪቬራ ሆቴል ባለቤት አቶ ዓለም ፍጹም ሲሆኑ የብድራቸው መጠን 2.4 ቢሊየን ብር መሆኑን የባንክ ምንጮች ይገልጻሉ።

አቶ ዓለም ፍጹም በከባድ የሌብነት ወንጀል ተጠርጥረው ከሳምንታት በፊት መታሰራቸው ታውቋል።

ይህ በኣንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ ዓመት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 አተረፍኩ ያለውን 14 ቢሊየን ብርም እንደገና በመከለስ ትርፉን ወደ 10 ቢሊየን ብር ዝቅ ማድረጉም ተመልክቷል።

ይህም ባንኩ በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ሳይኖረው ኤል ሲ በመክፈቱና በብር ምንዛሪ ለውጡ ሳቢያ የተከተለ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የውጭ ምንዛሪ ዘርፉ በዘፈቀደ የሚመራ መሆኑ በዚህ ረገድ ለተፈጠረው ክፍተት አስተዋጽኦ ማድረጉም ተመልክቷል።

ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ በሚያትምበት ወቅት በውክልና ለባንኮች ገንዘቡን የሚያሰራጨው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሆኑ ለቀናትም ቢሆን ገንዘቡ በባንኩ ሲንቀሳቀስ የሚያገኘው ጠቀሜታ ለባንኩ ድጋፍ እያደረገለት መሆኑንም ባለሞያዎቹ ይገልጻሉ።